ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምክር ቤቱን ጠቅላላ ጉባዔ አገደ

Ethiopian-chamber-of-commerce-meeting-stoppedFebruary 2, 2017 - የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊያካሂደው የነበረው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ ንግድ ሚኒስቴር ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡  

ለተከታታይ ወራት ውዝግብ ሲፈጥር የነበረው በንግድና ምክር ቤት ውስጥ እየታየ ያለው የሕግ ጥሰትና ተፈጸሙ የተባሉ ሕገወጥ ተግባራት እስኪጣሩ ድረስ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ሊካሄድ የነበረው ጉባዔና ምርጫ እንዲታገድ የተወሰነው ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ ቀደም ብሎ በንግድ ምክር ቤቱ አንዳንድ አባላት መረጃዎች ሲቀርብለት የነበረ ቢሆንም፣ ጣልቃ ላለመግባትና ጉዳዩ በንግድ ምክር ቤቱ እንዲቋጭ ሲመክር መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጥር 30 ቀን ሊካሄድ የነበረው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ታግዶ እንዲቆይ የሚገልጽ ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጠሩ የተባሉትን ችግሮች በራሱ መንገድ ለማጣራት መወሰኑንም ያመለክታል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱና በአባል ምክር ቤቶች መካከል በተፈጠረ የሐሳብ ልዩነት ጠቅላላ ጉባዔውን ምርጫ ለማካሄድ ባለማስቻሉ፣ ችግሩን ለመፍታት 18 አባል ምክር ቤቶች አጣሪ ግብረ ኃይል እስከማቋቋም መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡

ሆኖም አሁን እየታየ ያለው ችግር እየገዘፈና ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመምጣቱ፣ ከጠቅላላ ጉባዔውና ከምርጫው በፊት ንግድ ሚኒስቴር እጁን ለማስገባት እንደተገደደ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በ18 አባል ምክር ቤቶች ተቋቁሞ የነበረው አጣሪ ኮሚቴም የተፈጠሩ የሕግ ጥሰቶች ካሉ እንዲመረመሩ የሁለት ወራት ጊዜ ወስዶ ሲሠራ ከቆየ በኋላ፣ ሕግ በጣሱት ላይ ዕርምጃ ይወሰድ የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት በተለይ ከታች ሳይመረጡ በላይኛው እርከን የተመረጡ አመራሮች ካሉ ይህ ተጣርቶ ውሳኔ ይሰጥበት ብሎ የመጨረሻው ውሳኔ እየተጠበቀ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ አመራር ለመምጣት የአባሎቻቸውን ቁጥር ከፍ በማድረግ የቀረቡ አሉ በመባሉም ይህም ጉዳይ እንዲጣራ ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡

በዚህም ውሳኔ መሠረት በተደረገ ማጣራት ከ500 ሺሕ በላይ አባላት አለን ብለው ያስመዘገቡ አባል ምክር ቤቶች፣ በትክክል አባል መሆናቸውን የሚያረጋግጥና ንግድ ፈቃድ ሊቀርብባቸው ያልቻሉ ከ100 ሺሕ በላይ አባላት ተገኝተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ መረጃዎች እየተጠናከሩ ባለበት ወቅት ተጨማሪ የሕግ ጥሰቶች በአንዳንድ የምክር ቤቱ አመራሮች እየታየ በመምጣቱ፣ ጉባዔውም ለማካሄድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው ተብሎ ነበር ንግድ ሚኒስቴር የዕገዳ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ (ሪፖርተር)


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :