የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ ተሸጋግሯል

Light-Industry-City-Being-BuiltApril 21, 2017 - የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን ዓለም አቀፍ የቀላል ኢንዱስትሪ ግንባታ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩ የኋጂዬን ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዃሮን ጇን ገለጹ።

በጫማ ምርት የተሰማራው ኋጂዬን ግሩፕ በመስኩ የበቁ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞችን ለማፍራት በቻይና ሥልጠና እየሰጠ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ዃሮን ጇን ለኢዜአ እንደገለጹት በአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እየተካሄደ ያለው የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል።

ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ ግንባታ መሸጋገሩን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።

በአዲስ አበባ 137 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለው የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ "የፋብሪካዎች፣ የመንገድ፣ የውኃና የኃይል መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው" ብለዋል።

ሌሎች ሥራዎች በቀሪ ምዕራፎች እንዲከናወኑ በማድረግ የፓርኩ ግንባታ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም በዓመት 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ከ50-60 ሺህ ለሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል የማስገኘት አቅም ይኖረዋል።

በሴቶች ጫማ ምርት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ኋጂዬን ግሩፕ በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2012 ሥራውን የጀመረ ሲሆን ለአራት ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ያስገኘ የጫማ ፋብሪካ አለው።

በዚህ ፋብሪካው በቀን 6 ሺህ 500 ጥንድ ጫማዎችን በማምረት ለአውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የጀመረውን የኢንቨስትመንት ሥራ ለማስፋፋት የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እያከናወነ ነው።

ኋጂዬን ግሩፕ የኢትዮጵያን የጫማ ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በመስኩ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል ፕሬዚዳንቱ።

በዚህ ረገድ ኩባንያቸው 400 ኢትዮጵያዊያንን በቻይና ዶንጓን ከተማ በጫማ ዲዛይንና ምርት እንዲሁም በዘርፉ አስተዳደር በሦስት ዙሮች ሥልጠና መስጠቱን አስረድተዋል።

በአራተኛ ዙር ደግሞ 52 ኢትዮጵያዊያንን ተቀብሎ በቻይና ለአንድ ዓመት የተግባር ላይ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኩባንያው በቀጣይም በየዓመቱ 2 ሺህ አፍሪካዊያንን የማሰልጠን ዕቅድ እንዳለውና ከዚህ ውስጥ የበዙት ኢትዮጵያዊያን እንደሚሆኑ ይፋ አድርጓል። (ENA)


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :