ፎርብስ 5 ቀዳሚ የኢትዮጵያ ቢሊየነሮችን ይፋ አደረገ

Belayneh-KindieJune 17, 2017 - በየአመቱ የዓለም ባለፀጎችን የሃብት መጠን በማጥናት ደረጃቸውን ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መፅሄት  ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 5 የኢትዮጵያ ቢሊየነሮችን የሃብት መጠንና ደረጃ ከተሰማሩባቸው የንግድ ዘርፎች ጋር አወጣ ፡፡

በዚህም መሠረት ከ5ቱ ኢትዮጵያ ቁንጮ ባለሃብቶች መካከል በቅባት እህሎች ንግድ ላይ የተሠማሩት አቶ በላይነህ ክንዴ ከ60 ሚሊዮን ዶላር (1.3 ቢሊየን ብር) በላይ በማስመዝገብ  ቀዳሚው  ቢሊየነር ሊሆኑ በቅተዋል፡፡ በዚህ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አንዲት ሴት ባለፀጋም ተካተዋል፡፡ በ5ተኛ ደረጃ ላይ የሰፈሩት ወ/ሮ አኪኮ ስዩም አምባዬ ፤ ኦርቼድ ቢዝነስ ግሩፕ በተኘው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያቸው  ፤ ከ50 ሚሊዮን ዶላር (1.1 ቢሊየን ብር) በላይ አካብተዋል ብሏል -ፎርብስ፡፡

በዚህ ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አቶ በላይነህ ክንዴ የሃብት ምንጫቸው የግብርና ውጤት የሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ንግድ ሲሆን በ1997 ዓ.ም በተመሠረተው "በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ" በተሠኘው ኩባንያቸው አማካይነት በአመዛኙ በቅባት  ንግድ ላይ ተሠማርተው በ2016 እ.ኤ.አ  ከ60 ሚሊዮን  ዶላር በላይ ማግኘታቸውም ተጠቁሟል፡፡  ከዚህም  በተጨማሪ የባለሃብቱ ድርጅት ለውዝና ጣፋጭ ፍራፍሬዎችንም ጭምር ለገበያ እንደሚያቀርብ እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍም ተሠማርቶ ከመቶ በላይ የፈሳሽና ደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ባለቤት መሆን መቻሉንም ፎርብስ ጠቁሟል፡፡ 

በተያየዘም በቅርቡ ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያነት ያደገው የአቶ በላይነህ ክንዴ ድርጅት ፤ አንድ ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴል በባህርዳር ከተማ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የሆቴሉ ግንባታ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ አልቆ  ወደ ማጠናቀቂያ ስራ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ሆቴሉ  በአጠቃላይ 800 ሚሊዮን ብር ይፈጃል የተባለ ሲሆን ፤ የሆቴሉ ግንባታም የሆቴሉ  እህት ኩባንያ በሆነው በላይነህ ክንዴ ኮንስትራክሽን እየተካሄደ ነው፡፡

ከዚህ ግዙፍ ሆቴል በተጨማሪ አቶ  በላይነህ በአዲስ አበባ እና በአዳማ የሚገኙ የሁለት ሆቴሎች ባለቤት ናቸው፡፡ የመንግስት የነበረውን አዳማ ራስ ሆቴልን በ41 ሚሊዮን ብር ፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን ኢትዮጵያ ሆቴልን ከመንግስት በ94 ሚሊዮን በመግዛት በሁለቱም  ሆቴሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቀርፀው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ባለሃብቱ ሁለቱን ሆቴሎች እንደተረከቡ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ በማደስ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ በአዳማ ራስ ሆቴል ላይ ተጨማሪ 175 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ  የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ ሲሆኑ ፤ እየተገነቡ ያሉት  ሁለት ባለ ስድስትና ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ይህ የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅም ሆቴሉ መቶ የመኝታ ክፍሎች ያሉት ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ይሆናል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባውን  ኢትዮጵያ ሆቴልን በማፍረስም ባለሃብቱ ባለ 63 ፎቅ ግዙፍ ሆቴል የመገንባት ዕቅድ አላቸው፡፡

2ተኛ አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ
የአቶ ቴዎድሮስ ዋነኛ የሀብት ምንጫቸው የነዳጅ ንግድ ሲሆን የአምቦ የማዕድን ውሃ ኩባንያ ሊቀመንበርና ባለድርሻም ናቸው፡፡ ባለድርሻ የሆኑበት አምቦ ውሃ  በሃገሪቱ የማዕድን ውሃ ገበያውን የሚመራ ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን ባለሃብቱ ከዚህ ኩባንያ ዳጎስ ያለ ገቢ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ የተባለውን "ሣውዝ ዌስት ኤነርጂ" የተሠኘ ኩባንያ አቋቁመው፤ በጅግጅጋ አከባቢ ስፋት ባለው ቦታ ላይ በነዳጅ ማውጣትና ፍለጋ ላይ ተሠማርተዋል ተብሏል፡፡ ፎርብስ የባለሀብቱን የሀብት መጠን በአሃዝ አልገለፀም፡፡

3ተኛ ቡዛየሁ ተ/ቢዘኑ
የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናቸው የተገለፀው አቶ ቡዛየሁ፤ የሃብት ምንጫቸው የተለያዩ ንግዶች ናቸው ተብሏል፡፡ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ኩባንያዎች በመሪነት እንደሚቀመጥ የጠቀሰው ፎርብስ ፤ ኩባንያው የተሰማራባቸውን ዘርፎች ሲገልፅ፡- የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ አላቂ እቃዎች ምርት ፣ የሻይ ቅጠል ልማት፣ የማተሚያ ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርት ፣ ሪል ስቴት ፣ የሲሚንቶ ማምረትና የከሰል ድንጋይ ማዕድን ማውጣት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

4ተኛ ከተማ ከበደ
በሙስና ተጠርጥረው የፍርድ ሂደታቸውን ላለፉት 3 አመታት ገደማ በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ከተማ ከበደ ፤ በበርካታ የንግድ ዘርፎች ተሠማርተው የሚገኙ ሲሆን የሃብት መጠናቸው ከ 50 ሚሊዮን ዶላር (1.1 ቢሊየን ብር) እንደሚልቅ ተጠቁሟል፡፡

አቶ ከተማ ከበደ ኬኬ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር በተሠኘው ኩባንያቸው በዋናነት ብርድ-ልብስ እያመረቱ በመላው አፍሪካና በሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ፈጥረዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም በቃጫ ፣ድርና ማግ ምርት  እንዲሁም በከባድ ማሽነሪዎች ንግድ ላይ መሰማራታቸውን የጠቀሰው ፎርብስ ፤ የማዕድን ማውጫ መሳሪያዎችንም ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገቡም  ጠቁሟል፡፡ ባለሃብቱ በኮንስትራክሽን  በመንገድ ግንባታና ጥናት የተሰማሩ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚታወቁ የቡና ፣ ጥራጥሬና ቅመማ-ቅመም ላኪ ነጋዴዎች አንዱ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

5ተኛ ወ/ሮ አኪኮ ስዩም  
የ ወ/ሮ አኪኮ ዋነኛ የሀብት ምንጫቸው የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑን የጠቆመው ፎርብስ ፤ በኢትዮጵያ ካሉ ሴት ባለሃብቶች በቁንጮነት ተጠቃሽ ናቸው ብሏል፡፡ ኦርቼድ ቢዝነስ ግሩፕ የተሠኘው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያቸው በመንገድ ግንባታ ፣ በኮንስትራክሽን ቁሳቁሶች አቅርቦት እንዲሁም የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች በማከራየት ስራ ላይ ተሰማርቶ ባለሃብቷን ከ50 ሚሊየን ዶላር (1.1 ቢሊየን ብር) በላይ እንዲያካብቱ አድርጓል፡፡
  
 ምንጭ፡ አዲስ-አድማስ ጋዜጣ


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :