ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ለማቅረብ የመንግስት ይሁንታን እየጠበቀ ነው
July 10, 2017 - ቴዲ አፍሮ "ኢትዮጵያ" የተሠኘውን አልበም ካወጣ በኋላ ፤ በአዲስ አበባ የመጀመሪያውን ኮንሰርት ለማቅረብ የመንግስት ይሁንታን እየጠበቀ ነው፡፡
ድምጻዊው ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም ለአዲስ አመት ዋዜማ የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማቅረብ መዘጋጀቱን ማኔጀሩ አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡
ኮንሰርቱን አልበሙን ያከፋፈለው ኩባንያ ጆይ ኢቨንትስና ፕሮሞሽን ኩባንያ ከኤፕላስና ኤቨንት ፕሮሞሽን ኩባንያ ጋር በመተባባር የሚያዘጋጁት መሆኑን እና ጆይ ኤቨንትስ የሚሊኒየም አዳራሽን ከሚያስተዳድረው አዲስ ፓርክ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጆይ ኢቭንትስ ኮንሰርቱን ለማዘጋጀት የሚያስችል ዕውቅና ለማግኘት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ፈቃድ ማሳወቂያ ክፍል ጥያቄ ማቅረቡም ታውቋል፡፡ የአዲስ ፓርክ ዴቨሎፕመንትና ማኔጅመንት ኩባንያ የማርኬቲንግና የሰው ሃይል መምሪያሃላፊ አቶ ስለሺ ለማ ፤ ሰኔ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ለከንቲባ ፅህፈት ቤት በፃፉት ደብዳቤ ለአዲስ አመት ዋዜማ የሙዚቃ ኮንሰርት በሚሊኒየም አዳራሽ ለማካሄድ ፕሮግራም መያዙን ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የኮንሰርት ጥያቄ መቅረቡን አረጋግጠው ከሚመለከተው አካል ጋር ንግግር ከተደረገ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡
ለዚህ ኮንሰርት ቴዲ አፍሮ .8 ሚሊዮን ብር እንደሚከፈለው፣ ለሚሊኒየም አዳራሽ የዕለቱ ዝግጅት ኪራይ 1.2 ሚሊዮን ብር ክፍያ ለመፈፀም ስምምነት ላይ መደረሱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ቴዲ አፍሮ የአዲስ አበባውን ኮንሰርት ካካሄደ በኋላ ፤ በጎንደርና መቀሌ ከተሞች ተጨማሪ ኮንሰርቶች እንደሚያካሂድ ከስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር