August 14, 2017 - "ለውድድሩ በከፍተኛ ሁኔታ ስለተዘጋጀሁ መሐመድ ፋራህን እንደማሸንፈው እርግጠኛ ነበርኩ" ሲል በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች ለኢትዮጵያ ወርቅ ያስገኘው አትሌት ሙክታር እድሪስ ተናገረ።
እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በበኩሉ "አትዮጵያውያን አትሌቶች ይዘውት የገቡት የውድድር ዕቅድ እንድሸነፍ አድርጎኛል" ብሏል።
ትናንት ማታ በተደረገው የአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር በአትሌት ሙክታር እድሪስ አስገራሚ የአጨራረስ ብቃትና የአረንጓዴው ጐርፍ የሚለውን መጠሪያ ባስታወሰ የቡድን ስራ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች በጀርመን በርሊን በተካሄደው 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በርቀቱ ካስገኘው የወርቅ ሜዳሊያ በኋላ ትናንት ወርቅ ስታገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
14 አትሌቶች በተሳተፉበት የፍጻሜ ውድድር እንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት በተለያዩ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ተሰጥቶት ነበር።
ውድድሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጨረሻው 800 ሜትር አትሌቶች እያንዳንዱን የ400 ሜትር ርቀት የሄዱበት ፍጥነት ብዙም የከረረ አልነበረም።
በመጨረሻዎቹ 700 ሜትር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሙክታር እድሪስ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻና ሰለሞን ባረጋ፤ እንግሊዛዊው መሐመድ ፋራህ በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት አሜሪካዊ ፓል ቼሊሞ ተነጥለው በመውጣት ዙሩን ማክረር ጀመሩ።
የመጨረሻው ዙር ላይ መድረሳቸውን የሚያበስረው ደወል ሲደወል ኢትዮጵያኑ አትሌቶች ቀድመው በመውጣት ዙሩን አከረሩት፤ አትሌት ዮሚፍ ውድድሩ ሶስት መቶ ሜትር እስኪቀረው ድረስ በመምራት የመሐመድ ፋራህን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል።
አትሌት ሙክታር በመጨረሻዎቹ 300 ሜትሮች ፍጥነቱን በመጨመር በድንቅ አጨራረስ ውድድሩን አንደኛ በመውጣት ኢትዮጵያውያንን ደስ ያሰኘ ውጤት አስመዘግቧል።
በውድድሩ የቅድሚያ ማሸነፍ ግምት የተሰጠው ሞ ፋራህ የአትሌት ሙክታርን ፍጥነት መቋቋም ሳይችል ቀርቶ ሁለተኛ ሆኗል።
13 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ ከ79 ማይክሮ ሰከንድ አትሌት ሙክታር ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ ነው።
መሀመድ ፋራህ 13 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ከ22 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ፤ በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት አሜሪካዊ ፓል ቼሊሞ 13 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ከ30 ማይክሮ ሰከንድ በማጠናቀቅ ሶስተኛ ወጥቷል።
የቡድን ስራ በመስራት መሀመድ ፋራህ እንዲዳከም ያደረጉት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዮሚፍ ቀጄልቻና ሰለሞን ባረጋ በቅደም ተከተል አራተኛና አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
"ለውድድሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጅቼ ስለነበር መሐመድ ፋራህን እንደማሸንፈው እርግጠኛ ነበርኩ" አትሌት ሙክታር እድሪስ ከድሉ በኋላ የሰጠው አስተያየት ነው።
"መሐመድ ፋራህ 10 ሺ ሜትር ሮጦ ስለመጣ የድካም ስሜት ነበረበት በመጨረሻዎቹ ሜትሮች በፍጥነት የመጨረስ አቅም አልነበረውም በመጨረሻው ሰአት ጠንካራ የነበርኩ እኔ ነኝ" ብሏል ሙክታር።
"መሐመድ ፋራህ ብዙ ውድድሮችን አሸንፏል ነገር ግን አሁን እኔ ማሸነፍ ችያለሁ ለኢትዮጵያ አዲሱ ሻምፒዮን ነኝና ቀጣዩ ሻምፒዮን እኔ ነኝ" ሲል አትሌት ሙክታር ገልጿል።
በውድድሩ እስከ መጨረሻው ሰአት ለማሸነፍ ጥረት እንዳደረገ የገለጸው ሞ ፋራህ፤ "ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይዘውት የገቡት የውድድር እቅድና የቡድን ስራ እንድሸነፍ አድርጎኛል" ብሏል።
ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅና ሁለት ብር በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም አራተኛ ደረጃ ይዛለች።
Source: ENA