አትሌት ሻለቃ ዋሚ ቢራቱ የክብር ዶክትሬት አገኙ
August 27, 2017 - አትሌት ሻለቃ ዋሚ ቢራቱ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አገኙ።አትሌት ሻለቃ ዋሚ በሚሊኒየም አዳራሽ ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተላቸውን የክብር ዶክትሬት ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እጅ ተቀብለዋል።
አትሌት ዋሚ ቢራቱ ሃገራቸውን በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ወክለው ውጤታማ መሆን የቻሉ አንጋፋ አትሌት ናቸው። ዋሚ ቢራቱ በተወዳደሩባቸው የማራቶንና የረጅም ርቀት ሩጫዎች 80 ሜዳልያ ማግኘት ችለዋል።
ከዚህ ውስጥ 30 ወርቅ ሲሆን፥ 40 የብር እንዲሁም 10 የነሃስ ሜዳልያዎችን አሸንፈዋል።ዋሚ ቢራቱ ለኢትዮጵያ በማራቶን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ያመጣው አትሌት አበበ ቢቂላ ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸው ይነገራል።
አበበ ቢቂላ ውጤታማ በነበረበት የሮም ኦሊምፒክ በኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን አባል ቢሆኑም በህመም ምክንያት በውድድሩ ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል።በአሰልጣኝነትም አበበ ቢቂላን ማሰልጠን ችለዋል።
ባለፈው ጥር ወር 100ኛ አመታቸውን ያከበሩት አትሌት ሻለቃ ዋሚ ቢራቱ፥ 12 ልጆችና በርካታ የልጅ ልጆችን ማየት ችለዋል።የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ፥ በ22 የትምህርት አይነቶች ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 261 ተማሪዎችን ባስመረቀበት ስነ ስርዓት ላይ ነው የክብር ዶክትሬቱን ያበረከተላቸው።
ምንጭ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ