ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተጠየቀ

Agro-Industry-Park-EthiopiaAugust 27, 2017 - ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክን 12 ቢሊዮን ብር ብድር መጠየቁን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ልማት ባንክ በበኩሉ የቀረበልኝን የብድር ይሰጠኝ ጥያቄ በመፈተሽ ላይ ነኝ በቅርቡ ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል። በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የግብርና ምርቶች ባለባቸው አካባቢዎች 17 የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም በያዝነው ዓመት መጋቢት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በይርጋለም ፣ቡልቡላ ፣ ቡሬና ባዕኸር ላይ የአራቱን ፓርኮች የግንባታ መሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወቃል።

የፓርኮቹ የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በወቅቱ የፓርኮቹ መሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ መዘገባችን የሚታወስ ነው። ይሁንና ፓርኮቹን በተያዘላቸው ጊዜ ይጠናቀቃሉ ቢባልም እስካሁን ግንባታቸው አልተጀመረም፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ትራንስፎርሞሽን ዳሬክተር አቶ ሁነኛው አበባው ጉዳዩን አስመልክቶ እንዳሉት የአዋጭነት ጥናት፣ዲዛይኑን የመፈተሽና የግንባታ ውል መመሪያዎችን የማዘጋጀት ስራው ረጅም ጊዜ መውሰዱ ለፓርኮቹ ግንባታ መዘግየት ምክንያቶች ናቸው። ለአራቱ ፓርኮች ግንባታ 17 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚያስፈልግ ሲሆን መንግስት በድጎማ ለአራቱ ፓርኮች 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር አቅርቧል።

የተቀረውን የ12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የግንባታ ወጪ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር ለማግኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን የተናገሩት አቶ ሁነኛው የፓርኮቹን ግንባታ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ውስጥ እንደሚጠናቀቁም ተናግረዋል።ፓርኮቹን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ክልሎች ናቸው ያሉት አቶ ሁነኛው ለዚህም በየክልሎቹ የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽኖች መቋቋማቸው ነው የሚናገሩት።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና ፤የሊዝ ፋይናንስ ሃላፊ አቶ ተሾመ አለማየሁ በበኩላቸው ባንኩ የቀረበለትን የብድር ጥያቄ እየመረመረ በመሆኑ በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል። ባንኩ የፓርኮቹን ሼዶችና የመሰረተ ልማት ግንባታ የተሟላ ለማድረግ ፓርኩ ከሚገነቡባቸው ክልሎች የ20/80 ብድር እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በፓርኩ ውስጥ ለሚገቡ ባለሃብቶች ለማሽኖች ግዥና ለስራ ማስኬጃ ወጪዎች የብድር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ። በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች 80 በመቶ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማስገባት በመንግስት መታቀዱን ተከትሎ ባንኩ ይህን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በፓርኩ ለሚገቡ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በገንዘብም ሆነ በዓይነት የ15/85 ልዩ የገንዘብ ብድር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል መመቻቸቱንም አቶ ተሾመ ገልፀዋል።ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቾች ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነውን እሴት ያልተጨመረበት በመሆኑ ፓርኮቹ ይሕንን ችግር ለመፍታት አላማ ባደረገ መንገድ ይገነባሉ ተብሏል።

ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :