አምስተኛው አለም አቀፍ የ"ቱር መለስ" የብስክሌት ውድድር በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው
August 29, 2017 - አፍሪካንና አውሮፓን ያሳተፈ አምስተኛው አለም አቀፍ የ"ቱር መለስ" የብስክሌት ውድድር በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡ ውድድሩ በአለም አቀፍና በአፍሪካ ብስክሌት አሶሴሽን ከኢትዮጵያ የብስክሌት ፌደሬሽን፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ትግራይ እና ደቡብ ህዝቦች ክልሎች ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው፡፡
መነሻውን ሀዋሳ አድርጎ 120 ኪሎ ሜትርና አራት የውድድር አይነቶችን የሚሸፍነው የብስክሌት ውድድር ወንዶ ገነት፣ ሻሸመኔና ጥቁር ውሀ ከተሞችን ያካለለ ዛሬ ተካሂዷል፡፡ ነገ ደግሞ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ውድድር ይጀምራል፡፡
ከፍተኛ ፉክክር በታየበት መበጀመሪያው ውድድር ኢትዮጵያ 12 ተወዳዳሪዎች በማሳተፍ ተካፍላለች፡፡ ከኢትዮጵያ ሌላ በአፍሪካ ሩዋንዳ፣ ብሩኪናፋሶ፣ ኬኒያ፣ አልጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ጅቡቲ፣ ናይጄሪያና ጋና ከአውሮፓ ደግሞ የጀርመን ብስክሌተኞች ተሳትፈዋል፡፡
አሁንም ከአፍሪካ የግብፅ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የኮትዲቫር፣ የካሜሮን የዙምባዌ፣ የሱዳንና የታንዛኒያ ተወዳዳሪዎች የተካፈሉ ሲሆን በአጠቃላይ ከ140 በላይ ብስክሌተኞች ተፎካክረዋል፡፡
ውድድሩ የስቴጅ ፡ የዳገት፡ የቦላታና የወጣቶች በሚል በአራት ዓይነት የተከፋፈለ ሲሆን 40 ኪሎ ሜትር ቀዳሚ የውድድሩ አካል ሆኖ ቀሪው 80 ኪሎ ሜትር ውድድር አጓጊ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ኢትዮጵያ በአራቱም የውድድር ዓይነቶች አንደኛ በመውጣት ጥሩ ውጤት ስታስመዘግብ ኬኒያና ደቡብ አፍሪካ እንደቅደም ተከተላቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡
በአራቱም ዓይነት ውድድሮች ሬድዋን ኢብራሂም ከኢትዮጵያ አንደኛ፣ ሳን ሳሊም ከኬኒያ ሁለተኛ እና ጃአኮ ስፔንት ዊለር ከደቡብ አፍሪካ ቀጣዩን ደረጃ በመያዝ አሸንፈዋል፡፡ የደቡብ ህዘቦች ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ እንዳሉት ውድድሩ በአለም አቀፍ ደረጃ በክልሉ ሲካሄድ የመጀመሪያና ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የአሮሚያና ደቡብ ህዝቦች ለብስክሌተኞቹ ያደረጉት አቀባበልና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የመጀመሪያው ዙር ውድድር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ የውድደሩ መጨረሻ አዲስ አበባ ሲሆን ነሐሴ 25/2009ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡
ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ