ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ስኳር ኤክስፖርት አደረገች - ስኳር ኮርፖሬሽን

Sugar-Corporation-EthiopiaSeptember 1, 2017 - የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ስኳር ኤክስፖርት ተደረገ፡፡ መንግሥት ከኬንያ መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል ለስኳር ኮርፖሬሽን በሰጠው መመርያ መሠረት 43 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ኬንያ ተልኳል፡፡ስኳር ኮርፖሬሽን በ2003 ዓ.ም. ከመቋቋሙ በፊት የአውሮፓ ኅብረት ለታዳጊ አገሮች ከጦር መሣሪያ በስተቀር የሚያመርቱትን ምርት ከቀረጥ ነፃ እንዲልኩ በሚሰጠው  ዕድል፣ ኢትዮጵያ ያላለቀለት ስኳር ወደ አውሮፓ ትልክ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚያ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ ስኳር ወደ ውጭ መላከ ከማቋረጧም በላይ፣ በአገር ውስጥም ከፍተኛ የስኳር እጥረት በመከሰቱ እስከ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ድረስ ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች፡፡የስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከኬንያ መንግሥት በቀረበላት ጥያቄ መሠረት 43 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ውጭ ልካለች፡፡

‹‹የኬንያ መንግሥት ጥያቄ የመጣው ኮርፖሬሽኑ በጥሩ ዋጋ ኤክስፖርት ለማድረግ፣ በአገር ውስጥ እጥረት ከተፈጠረም ኢምፖርት ለማድረግ ባቀደበት ጊዜ ነው፤›› በማለት አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኬንያ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ሁነኛ መዳረሻ መሆን ጀምራለች፡፡ በተለይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኬንያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በድርቅ ከተመቱ በኋላ ኢትዮጵያ ለኬንያ ገበያ በቆሎ አቅርባለች፡፡

የኬንያ ገበያ ከበቆሎ በተጨማሪ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርት ለሆነው ስኳር ሁነኛ መዳረሻ መሆኑ እንደታመነበት አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥለው 2010 በጀት ዓመት ነባሮቹን ጨምሮ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ይገባሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 6.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡የአገሪቱ የስኳር ፍላጎትም ከዚሁ ምርት ጋር የሚቀራረብ በመሆኑ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ጥሩ ዋጋ በሚገኝበት ወቅት ወደ ውጭ ለመላክ፣ እጥረት በሚፈጠርበት ወቅት ደግሞ ከአራማጭ ገበያዎች ወደ አገር ለማስገባት አቅዷል፡፡

ከ43 ሺሕ ኩንታል በተጨማሪ ስኳር ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ የስኳርና የተለያዩ የስኳር ተረፈ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የጥራት ሰርተፊኬት  የምርት መለያ (ብራንድ) ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች በዕድሳት ላይ በመሆናቸው ሥራ አቁመዋል፡፡ ይሁንና እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ በቂ አቅርቦት አለ፡፡

ስኳር እየተከፈፈለ የሚገኘው ንግድ ሚኒስቴር በሚያወጣው ኮታ መሠረት በሸማች ማኅበራት፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በኢትፍሩትና በቀድሞ ጅንአድ አማካይነት ነው፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :