የአዲስ አበባ አስተዳደር የቴዲ አፍሮ አልበም ምረቃ ፕሮግራም ወቅቱን የጠበቀ የዕውቅና ጥያቄ አልቀረበለትም አለ

Teddy-Afro-ConcertSeptember 8, 2017 - እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ እንደሚመረቅ ቀን የተቆረጠለት የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አልበም ምርቃት ፕሮግራም፣ ወቅቱን የጠበቀ የዕውቅና ጥያቄ እንዳልቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ረዳትና የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ክፍል ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ተስፋ ዋቅጅራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሒልተን አዲስ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የአልበም ምረቃ ለማካሄድ ጥያቄ የያዘውን ደብዳቤ የተመለከቱት ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

‹‹ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ ቀኑ 9፡30 ድረስ ቢሮ ነበርኩ፡፡ የቀረበ ደብዳቤ የለም፡፡ በነጋታው ዓርብ የኢድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ስለነበር ሥራ የለም፡፡ ሰኞ ቢሮ ስገባ ደብዳቤውን አግኝቻለሁ፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ቀኑ አልፏል፤›› ሲሉ ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት የቀረበው ጥያቄ ዘግይቶ መድረሱን አቶ ተስፋ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥያቄ ሊቀርብ የሚገባው ከፕሮግራሙ በፊት በሥራ ቀናት ከ24 ሰዓት ቀደም ብሎ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአልበም ምረቃው ፕሮግራም ጥያቄ ግን ይህንን አካሄድ ያላገናዘበ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ለአልበሙ ምረቃ የዕውቅና ጥያቄ ማቅረብ ለምን ያስፈልጋል? በአገሪቱም ሆነ በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች፣ ልዩ ልዩ ስብሰባዎችና የአልበም ምረቃዎች ጭምር የዕውቅና ጥያቄ ቀርቦላቸው አያውቅም፡፡ ይህንን ምን አዲስ አደረገው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለአቶ ተስፋ አቅርቦላቸዋል፡፡

አቶ ተስፋ እንደሚሉት፣ ሠርግና የመሳሰሉት ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሥነ ሥርዓቶች ግን ጥያቄ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ ‹‹በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር ይህ የሰላማዊ ሠልፍና የሕዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ክፍል የተቋቋመው ለዚህ ዓላማ ነው፡፡ ያለበለዚያ ለምን ክፍሉ ያስፈልጋል?›› ሲሉ አቶ ተስፋ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡

የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም ምረቃ ፕሮግራም ያዘጋጁት ጆርካ ኢቨንት፣ ጆይስ ኢቨንትና ዳኒ ዳቪስ ናቸው፡፡ አዘጋጆቹ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው ይህንን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከሒልተን አዲስ ጋር ስምምነት አድርገውና ክፍያ ፈጽመው ቀኑን በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡

ነገር ግን የሒልተን አዲስ አበባ የጥበቃ ኃይል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ለጥበቃና ለትራፊክ እንቅስቃሴው ዕገዛ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አዘጋጆቹን በመጥራት ሐሙስ ጠዋት ውይይት ማድረጋቸውን፣ በዚህ ውይይት ላይ አዘጋጆቹ የዕውቅና ደብዳቤ እንዳላቸው ሲጠየቁ ፕሮግራሙ የተለየ እንዳልሆነና የዕውቅና ጥያቄ እንደማያስፈልገው መከራከሪያ ማቅረባቸውን ከአዘጋጆቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ነገር ግን ፖሊስ የዕውቅና ፈቃድ እንደሚያስፈልግና የዕውቅና ፈቃድና ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል በሌለበት ፕሮግራሙ ሊካሄድ አይችልም በሚለው አቋሙ በመፅናቱ፣ አዘጋጆቹ በመጨረሻው ሰዓት የዕውቅና ደብዳቤያቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የጆርካ ኢቨንት ባለድርሻ አቶ አጋ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጆርካ ኢቨንት ስምንት ትልልቅ ፕሮግራሞችን ሲያካሂድ ተመሳሳይ የዕውቅና ጥያቄ አልተጠየቀም፡፡

‹‹ነገር ግን ይሁን ብለን ለሥነ ሥርዓቱ (ፎርማሊቲ) ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን ደብዳቤ አስገብተናል፤›› በማለት ገልጸው፣ ይህንን ሁሉ ርቀት ከሄዱ በኋላ ፕሮግራሙ ሳይካሄድ በመቅረቱ የሞራል ስብራት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ትልልቅ ዝግጅቶችን የማዘጋጀት ልምድ ገና አልካበተም፡፡ ጆርካ ኢቨንት ይህንን ለመሙላት ነው የተቋቋመው፡፡ ነገር ግን ውኃ የማያነሱ ምክንያቶችና መሰናክሎች መብዛታቸው ከገንዘብ የበለጠ ሞራል የሚነኩ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ አጋ በቅሬታ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሦስቱ አዘጋጆች ተነጋግረው የሚደርሱበትን ውሳኔ እንሚያሳውቁ አቶ አጋ ተናግረዋል፡፡ ውሳኔውን ግን አሁን ለመተንበይ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ቴዲ አፍሮ ይህ ፕሮግራም መካሄድ አለመቻሉን በተመለከተ በፌስቡክ ገጹ እንዳመለከተው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበም ምርቃት አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ ተጠናቆና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የመግቢያ ወረቀት ታድሎ ካበቃ በኋላ፣ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ጉዳዩ ይመለተከኛል የሚለው የመንግሥት አካል መርሐ ግብሩን ለማካሄድ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ዝግጅቱ እንዳይካሄድ መከልከሉን ለክቡራን ወገኖቻችን ስናሳውቅ የተሰማንን ከፍተኛ ሐዘን በመግለጽ ነው፤›› በማለት የተፈጠረውን ሁኔታ አስረድቷል፡፡ የአልበሙ ምርቃት የመሰረዝ ዜና ከተሰማ በኋላ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

Source:- Reporter


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :