ሐዋሳ፣ ቦሌ ለሚና ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርኮች 248 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኙ - ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
September 15, 2017 - የሐዋሳ ፣ ቦሌ ለሚና ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርኮች 248 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘታቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለፀ።ከዚሁ ገቢ 200 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው ስራ ከጀመረ አራት ወራትን ያስቆጠረው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። በውስጡ 52 ፋብሪካዎችን የያዘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በግዙፍነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን ከዓለም ግዙፍ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች መካከልም ይጠቀሳል።
ቦሌ ለሚና ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በ2009 በጀት ዓመት እያንዳንዳቸው 24 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።
ፓርኮቹ ከ31 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎችም አዲስ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ኢትዮጵያን በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ጥረት ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ በስፋት እንደሚሰራ ኮሚሽነር ፍጹም አመልክተዋል።
የግብርናና ምርቶች ፣ ማኑፋክቸሪንግ ፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ጫማና የቆዳ ውጤቶች ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
"በእነዚህ ዘርፎች ጠንክረን ከሰራንና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱን አጠናክረን ከቀጠልን ፤ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የማንደርስበት ምክንት የለም" ነው ያሉት ኮሚሽነር ፍጹም።
በ2010 በጀት ዓመት የተሻለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ ለአበባ እንዲሁም ለጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ምርቶች የሚሆን ቦታ መዘጋጀቱንም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት የውጭ ባለኃብቶችን በመሳብ ከዓለም ቬትናምን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ያም ሆኖ በ2009 በጀት ዓመት ከዘርፉ የወጪ ንግድ 271 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 89 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ነው።
የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ የባለኃብት ምልመላ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት 10 ፓርኮች በመንግሥት እየተገነቡ ሲሆን፤ ኃይጁን፣ ጆርጅ፣ አረርቲ እና በድሬዳዋ ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ጨምሮ አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በግል ባለኃብቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
ቻይና፣ ሕንድ፣ ቱርክ፣ ሱዳንና አሜሪካ ባለ ኃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ በቅደም ተከተል ቀዳሚውን ሥፍራ ይዘዋል።
ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ