ሙክታር የጂሮ አል ሳስ የጎዳና ሩጫ ውድድር አሸነፈ

Muktar-Edris-EthiopiaOctober 1, 2017 - አትሌት ሙክታር እድሪስ ትናንትና በተካሄደው የጂሮ አል ሳስ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድርን አሸንፏል፡፡ በጣልያን ትሬንቶ ከተማ የተካሔደውን ውድድር አትሌት ሙክታር እድሪስ በ28 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል። ውድድሩን ሲያሸንፍ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጥላሁን ሃይሌ ከአትሌት ሙክታር በአንድ ሰከንድ ዘግይቶ ሁለተኛ ሲወጣ፤ አትሌት ሀሰን ሀጂ 29 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ በመግባት ሶስተኛ በመውጣት የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የበላይነት አረጋግጧል። አትሌት ሙክታር እድሪስና ጥላሁን ሃይሌ እስከ ውድድሩ ማብቂያ ድረስ ትንቅንቅ አድረገዋል።

አትሌት ሙክታር ውድድሩን በአስገራሚ የአጨራረስ ብቃት ማሸነፉን  የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል። "በከፍታ ቦታ ላይ ያደረኩት ልምምድ ውድድሩን እንዳሸንፍ አግዞኛል" ሲል አትሌት ሙክታር ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ በሰጠው አስተያየት ገልጿል።

"ብቃቴ ከዕለት ዕለት እየተሻሻለ ነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ድል ህይወቴን ቀይሮታል ፤ ያለኝን ወቅታዊ ብቃት ይዤ ለመቀጠል ጠንክሬ እሰራለሁ " በማለት ባገኛቸው ድሎች ቤተቡንና አገሩን ማኩራቱን ገልጿል።

በትሬንቶ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ታጅቦ መወዳደር ደስታን የሚሰጥ ነው" ሲል አትሌት ሙክታር አክሏል።

አትሌት ሙክታር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአምስት ሺ ሜትር አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።አትሌት ሙክታር እ.ኤ.አ በ2014 እና በ2015 የጂሮ አል ሳስ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድርን ማሸነፉ በመረጃው ለትውስታ ተጠቅሷል።የጂሮ አል ሳስ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ለወንድ አትሌቶች ብቻ የሚዘጋጅ ውድድር ነው።

እ.ኤ.አ ከ1945 ጀምሮ እሰከአሁን ያለማቋረጥ ተካሂዷል።

ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :