ኢትዮጵያ የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ አላቀረብኩም አለች
October 2, 2017 - ኢትዮጵያ የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ምንም አይነት ጥያቄ አለማቅረቧን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገለጸ።
የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ጥያቄ ማቅረቧን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። የአገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ውድድር፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ጥያቄ ማቅረባቸውን ኮንፌደሬሽኑ አስታውቋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እንደገለጹት የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ለካፍ ያስገባነው ሰነድ የለም ብለዋል።
ውድድሩን ለማስተናገድ ኬኒያ የተመረጠች ቢሆንም በቂ ዝግጅት እያደረገች ባለመሆኑ የአስተናጋጅነት መብቷ መነጠቋን ተከትሎ ውድድሩን እናዘጋጅ ወይስ አናዘጋጅ? በሚል ውይይት እንደተደረገ ገልጸው ነገር ግን ውድድሩን ለማስተናገድ በይፋ የቀረበ ጥያቄ እንደሌለ ገልጸዋል።
በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ በ2020 የሚካሄደውን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ናት፤ የአሁኑን ውድድር ለማዘጋጀት ጥያቄ ከምናቀርብ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚካሄድው ውድድር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባል የሚል ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ያስረዱት አቶ ጁነዲን።
ውድድሩ ከሶስት ወር በኋላ ነው የሚካሄደው ለዛም የሚሆኑ ስታዲየሞችና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ባለው ጊዜ ለማዘጋጀት ስለማይቻል ለ2020ው ውድድር ትኩረት መደረግ እንዳለበት ውሳኔ መተላለፉን አብራርተዋል።
ካፍ መረጃውን ከየት አምጥቶ ነው ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች ያለው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባለች የሚለውን መረጃ ከየት እንዳመጣው የምናውቀው ነገር የለም" ሲሉ አቶ ጁነዲን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2020 የሚካሄደውን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ውድድር እንድታዘጋጅ ከአንድ ዓመት በፊት በይፋ መመረጧን አስታውሰዋል።
የካፍ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በ2018 የሚካሄደውን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ሌላ አገር እንዲያስተናግድ በ15 ቀናት ውስጥ አዲስ አዘጋጅ አገር እንዲመረጥ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
የአገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ 16 አገሮች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ የዘንድሮው ውድድር ለአምስተኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።
ኢዜአ