የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት አንድ ቢሊዮን ብር መደበ

Ethiopia-renewable-energyOctober 5, 2017 - በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የታዳሽ ኃይል ልማት ፕሮጀክቶች የአውሮፓ ኅብረት የአንድ ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተከፈተው የታዳሽ ኃይል ልማት ጉባዔ ንግግር ያደረጉት የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ዩሃን ቦርግስታም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የታዳሽ ኃይል ልማት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ልማት ዋና አካል አድርጎ መቅረፁን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የኢንዱስትሪ ልማት የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና እንዳለው የገለጹት ሚስተር ቦርግስታም፣ መንግሥት ለታዳሽ ኃይል ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ 90 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጨው ከውኃ ኃይል ነው፡፡ የተለያዩ የንፋስ፣ የፀሐይና የጂኦተርማል ልማት ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ በአርዓያነት ልትጠቀስ የምትችል አገር ናት፤›› ብለዋል፡፡

ሚስተር ቦርግስታም የአውሮፓ ኀብረት በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የአውሮፓ ኅብረት 830 ሚሊዮን ብር (30 ሚሊዮን ዩሮ) ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፣ በዚህም ከ400,000 በላይ የገጠር ነዋሪዎች የባዮ ጋዝ ኃይል ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ለሚካሄዱ የኃይል ልማት ፕሮጀክቶች ኅብረቱ አንድ ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዩሮ) መመደቡን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ሪኒውዌብል ኢነርጂ ሶሉሽንስ ፎር አፍሪካ›› በተባለው ተቋም በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከታዳሽ የኃይል ምንጭ (ውኃ፣ ንፋስ፣ ፀሐይና ጂኦተርማል) 60,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ዕምቅ ሀብት እንዳላት ገልጸው፣ መንግሥት ግልጽ የሆነ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የታዳሽ የኃይል ምንጭ በማልማት ወደ ጎረቤት አገሮች ንፁህ የኤሌክትሪክ ኃይል መላክ መጀመሯን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት ድባብ የፈጠረ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ እንዲሰማራ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ኢንቨስትመንት እንጂ ዕርዳታ አንፈልግም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ምቹ ኢንቨስትመንት ሁኔታ ተጠቅመው ኢንቨስት ቢያደርጉ ራሳቸውን ጠቅመው በርካታ የሥራ ዕድል ለወጣቶች በመፍጠር፣ ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ስደት መቀነስ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙ የአውሮፓ የኢነርጂ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ መብራህቱ መለስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱን በአፍሪካ በቀላል ማምረቻ ዘርፍ ቀዳሚ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ልማት መርሐ ግብር ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመገንባት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የታዳሽ የኃይል ምንጮችን በማልማት በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ለአምራች ኢንዱስትሪው በማቅረብ ላይ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡

የታዳሽ የኃይል ምንጭ ልማት አካባቢን የማይበክል አማራጭ የኃይል ምንጭ በመሆኑ፣ በተለይ የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ የንፋስ፣ የፀሐይ ኃይልና የጂኦተርማል ኃይል ልማት ፕሮጀክቶችን ማልማት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በኃይል ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ የፋይናንስ ጉዳይ ትልቅ ፈተና እየሆነበት እንደመጣ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የታዳሽ ኃይል ምንጭ ልማት ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የአውሮፓ ኩባንያዎች ለማከናወን ላሰቧቸው ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ምንጭ ከየት ይመጣል ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው፣ እስካሁን መንግሥት በኃይል ልማት ዘርፍ ከራሱ ካዝናና ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ተበድሮ ሲገነባ መቆየቱን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ግን የግሉ ዘርፍ በኃይል ልማት እንዲሳተፍ ሁኔታዎች እንዳመቻቸ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የውጭ አልሚዎች የኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት የራሳቸውን የፋይናንስ ምንጭ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :