ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ይፋለማሉ
October 21, 2017 - በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን አገናኝቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አንድ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ማምሻውን ተካሂዷል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመስዑድ መሐመድ ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 በመርታቱ፥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በፍጻሜው ይፋለማሉ።
ትናንት በነበረው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ጂማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገናኝተዋል።
በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ ከስታዲየሙ ውጪ የሚገኝ ትራንስፎርመር ፈንድቶ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር።
ጨዋታው 82ኛው ደቂቃ ላይ ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ ተጀምሮ ተጠናቋል።ጨዋታው ያለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎም ቡድኖቹ ወደ መለያ ምት አምርተዋል።
በተሰጠው የመለያ ምትም ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ለ 2 በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።
ለፍፃሜ ያለፉት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በመጪው እሁድ ለዋንጫ የሚያደርጉት ፍልሚያ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል።
ኤፍ.ቢ.ሲ