ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ ወደ ውጪ ከተላከ ቡና 215 ሚሊየን ዶላር አገኘች
October 28, 2017 - 2010 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ ቡና 215 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን ገለፀ።
ገቢው በሩብ ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላከ 55 ሺህ 825 ቶን የቡና ምርት የተገኘ ሲሆን፥ በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ የ34 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብልጫ አለው ተብሏል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትለከው ምርት 25 በመቶውን ገቢ የምታገኘው ከቡና ምርት መሆኑን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ሀገሪቱ ቡናን ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡ አምስት ሀገራት አንዷ ብትሆንም፥ ከዘርፉ ያቀደችውን ያህል ጥቅም አግኝታ አታውቅም።
በሩብ ዓመቱ 56 ሺህ 550 ቶን ቡናን ለዓለም አቀፍ ገቢያ በማቅረብ እስከ 245 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም 215 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው ማሳካት የተቻለው።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር፥ ከባለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ያለውን ልዩነት በማሳያነት ጠቅሰው በዘርፉ ለውጦች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።
ዘንድር ገቢው እና አቅርቦቱ የጨመረው የተጀመሩ አዳዲስ የግብይት ስርዓቶች ህገ ወጥ የቡና ንግድን ማስቀረት በመቻሉ ነው ብለዋል።
የግብይት ስርዓቱ ምርቱ ወደ መጋዘን ሳይገባ በመኪና ላይ እንዳለ መሸጥን የሚያስችል መሆኑ፥ የምርት ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ ባሻገር አርሶ አደሮች የግብይት መስፈርቱን ካሟሉ በቀጥታ መገበያየት እንዲችሉ እድል ይሰጣቸዋል።
አሁን ላይ 37 የሚደርሱ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ወደ ውጪ ገበያ መላክ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን ገልጿል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በቡና ግብይቱ ላይ የአሰራር ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ባለፉት ሶስት ወራት የቡና የወጪ ንግድ መነቃቃት አሳይቷል ብለዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ባለፈው ዓመት 11 ሺህ ቶን ቡና በህገ ወጥ መንገድ ወደ ገቢያ ሲገባ መያዙን ተናግረው፥ አዲሱ የግብይት ስርዓት የዘርፉን ችግሮች በመቀነስ በቡና ምርት እና በሚገኘው ገቢ ላይ ለውጦችን ማምጣት የሚያስችሉ ምልክቶችን አሳይቶናል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 270 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም አቀፉ ገቢያ በማቅረብ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከለማግኘት ታቅዷል።
ባለስልጣኑ የዘንድሮ እቅዱን ለማሳካት ዓለም አቀፍ የቡና አውደ ርእዮች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ቡና ፈላጊ ሀገራት ቁጥርን ለማሳደግ ይሰራል ብሏል።
ባለፈው ዓመት 225 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ 882 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ ይታወቃል።
ምንጭ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ