የውጭ ምንዛሬ ማስተካከያ መደረጉን ተከትሎ ሆነ ብለው ምርት የደበቁ የ39 ነጋዴዎች መጋዘኖች ታሸጉ
October 29, 2017 - በአዲስ አበባ ከተማ የብር ውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያ መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ ምርቶችን የለም በማለት ያለአግባብ ያከማቹ 39 ነጋዴዎች መጋዘኖች መታሸጋቸው ተገለፀ።
ከእነዚህ 39 ነጋዴዎች መካከል ስምንቱ ከፍተኛ አስመጪ ነጋዴዎች መሆናቸውን የአዲስ አባባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል።
ከአስመጪዎች መካከል የብእርና የአገዳ ሰብሎች አስመጪ ሚፍታህ አብዱራሃማን፣ እስማኤል ፒ.ኤል.ሲ፣ ሙክታር አብዲ፣ ይልማ አግሪ ቢዝነስ እና መንሱር ሽፋ ይገኙበታል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አማካሪ አቶ መከታ አዳፍሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ቢሮው ከጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከአጋር አካላት ጋር ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር ነው መጋዘኖቹ የታሸጉት።
በታሸጉ መጋዘኖች ውስጥ የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን፣ የግብርና ምርቶች ማለትም 40 ሺህ ኩንታል ሩዝ፣ 200 ሺህ ኩንታል ዛላ በርበሬ፣ 30 አይሱዙ ተሽከርካሪ፣ የታሸጉ የለስላሳ መጠጦች እና በርካታ የህጻናት ንፅህና መጠበቂያዎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም መንግስት ለህብረተሰቡ በድጎማ ሸቀጣሸቀጦችን አየር በአየር በከፍተኛ ጭማሪ ሲሸጡ የነበሩ 23 ነጋዴዎች ሱቅም ታሽጓል።
በዚህም በኮልፌ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተያዙት 23 ነጋዴዎች፥ 715 ጀሪካን ዘይት እንዲሁም በርካታ ኩንታል የስንዴ ዱቄት እና ስኳር በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሲሸጡ ነው የተያዙት።
እንደ አቶ መከታ ገለጻ የተያዙት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በድጎማ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፥ በቀጣይ በታሸጉት ሱቆች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ምንጭ፦ FBC