ካፍ ኢትዮጵያ ወደ ቻን እድትመለስ የሚያስችላት ሁለተኛ እድል ሰጠ
October 29, 2017 - የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በ2018 በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ቻን ውድድር ላይ እንድትካፈል የሚያስችላት ሁለተኛ እድል ሰጠ።
የ2018 የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ያለፉ 16 ሃገራት አስቀድመው ቢታወቁም፤ ካፍ የግብፅን አለመካፈል ተከትሎ የምስራቅ እና መካከኛው አፍሪካ ዞን አንድ ተጨማሪ ሀገር ለውድድሩ እንዲያልፍ ወስኗል።
በመጨረሻው የማጣሪያ ዙር የወደቁት ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የደርሶ መልስ ጨዋታ አድርገው ወደ ሞሮኮ እንዲያመሩም ካፍ ዳግመኛ እድል ሰጥቷቸዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን፤ ሩዋንዳ ደግሞ በዩጋንዳ ተሸንፈው ነው ከውድድሩ ውጪ መሆናቸው ይታወሳል።
ግብፅ የሊግ ውድድሯን ላለሟቋረጥ እና ለዋናው ብሄራዊ ቡድኗ የዓለም ዋንጫ መዘጋጃ ሰፋ ያለ ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከቻን እራሷን ማግለሏን ተክተሎ ከሰሜን ዞን አልጄሪያ ትሳተፋለች ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ሳይሆን በመቅረቱ እድሉ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ዞሯል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የካፍ የሚዲያ ኃላፊ ጁኒየር ቢኒያም፥ “እድሉ መሰጠት የነበረበት ከሰሜን ዞን ላለ ቡድን ነበር፤ ነገር ግን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ እንዲጫወቱ ወስኗል” ብለዋል።
ጁኒየር ለምን የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ውሳኔውን ለመወሰን እንደቻለ ከመጥቀስ ግን ተቆጥቧል።
ኢትዮጵያ ሩዋንዳን ጥቅምት 26 አዲስ አበባ ላይ ስታስተናግድ የመልስ ጨዋታው ከሳምንት በኃላ ህዳር 3 ኪጋሊ እንደሚጫወቱ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።
ኢትዮጵያ በ2014 ለቻን ለመጀመሪያ ግዜ ስታልፍ ሩዋንዳን በመለያ ምት አሸንፋ መሆኑ አይዘነጋም፡፡
ጀርመናዊው የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አንቶኒ ሄይ ለዝግጀት 24 ተጫዋቾችን ከወዲሁ የጠሩ ሲሆን እሁድ ዝግጅት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ በኩል ያለው ሁኔታ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ምንጭ፦ Soccer Ethiopia