ፓርቲዎቹ ቅይጥ የምርጫ ስርዓቱ 80 በመቶ አብላጫ፣ 20 በመቶ ተመጣጣኝ ድምፅ ያጣመረ እንዲሆን ተስማሙ

Ethiopia-Election-ReformNovember 3, 2017 - የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት 80 በመቶ አብላጫ፣ 20 በመቶ ተመጣጣኝ ድምፅ ያጣመረ "ቅይጥ የምርጫ ስርዓት" እንዲሆን ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተስማሙ።

ገዢው ፓርቲን ጨምሮ 16 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ህግ 532/99 ላይ ዛሬ ለስምንተኛ ጊዜ ባካሄዱት ድርድር የቅይጥ የምርጫ ስርዓትን የመቶኛ ድርሻ ወስነዋል።

ከሁለት ቀን በፊት በተካሄደው ድርድር በጋራ ተጣምረው የሚደራደሩት 11 ፓርቲዎች የተፈጠረውን ልዩነት በተመለከተ መክረው ለመምጣት ቀጠሮ ይዘው ነበር።

በዛሬው ድርድርም “60 በመቶ አብላጫና 40 በመቶ ተመጣጣኝ ያጣመረ ቅይጥ የምርጫ ስርዓት ይሁን” የሚለው አቋማችን እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ለድርድሩ ውጤታማነት ገዢው ፓርቲ ባቀረበው ተስማምተናል ብለዋል።

የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲና የመላው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም 80 በመቶ አብላጫና 20 በመቶ ተመጣጣኝ ድምፅ ያጣመረ ቅይጥ የምርጫ ስርዓት ይኑር የሚል አቋም መያዛቸውን ገልፀዋል።

በዚሁ መሰረት አገሪቱ 80 በመቶ አብላጫና 20 በመቶ ተመጣጣኝ ድምጽ ያጣመረ ቅይጥ የምርጫ ስርዓት ይኑራት የሚለው የገዢው ፓርቲ ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ተደራዳሪዎቹ ፓርቲዎች ከስምምነት ደርሰዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ምርጫ የሚያዙ 550 ወንበሮችና በተመጣጣኝ ድምፅ ምርጫ የሚያዙ 110 ወንበሮች በድምሩ 660 ወንበሮች ይኖሩታል።

በተመጣጣኝ ምርጫ ለሚያዙ ወንበሮች ፓርቲዎች ሲወዳደሩ አንድ ክልል እንደ አንድ የምርጫ ጣቢያ እንዲወሰድና በተመሳሳይ በከተማ አስተዳደር ደረጃም እንደ አንድ የምርጫ ጣቢያ እንዲሆን ከስምምነት መድረሳቸው ይታወቃል።

በመሆኑም ፓርቲዎች በ'ሄር ኮታ' ስርዓት ማለትም በክልል ደረጃ የሚያገኙት ድምፅ በክልሉ በተመጣጣኝ ምርጫ ለሚያዙት ወንበሮች እየተካፈለ ህዝቡ በሰጣቸው ድምፅ መሰረት ወንበር የሚያገኙ ይሆናል።

በሌላ ዜና ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርድ አወቃቀርና አደረጃጀት ላይ ባካሄዱት ድርድር መስማማት ሳይችሉ በቀጠሮ ተለያይተዋል።

ልዩነት ከፈጠሩ ሃሳቦች መካከል ዋናዎቹ የምርጫ ቦርድ ስያሜና የቦርድ አባላት አመራረጥ የሚሉት ናቸው።

የአሥራ አንዱ ፓርቲዎች ጥምረት የምርጫ ቦርድ ስያሜ ወደ ምርጫ ኮሚሽን መቀየሩ ተአማኒነት እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉ ተከራክረዋል።

ገዢው ፓርቲ በበኩሉ የቦርዱን ስያሜ መቀየር በራሱ ለውጥ አያመጣም፣ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ቦርዱን በማጠናከርና ይዘቶችን  በማሻሻል ነው የሚል አቋም ይዟል።

ፓርቲዎቹ ይህን ጨምሮ የምርጫ ቦርድ አወቃቀርና አደረጃጀት ላይ ለመደራደር ለጥቅምት 29 ቀን 2010  ቀጠሮ ይዘዋል።

በዕለቱ ገዢው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን በተመለከተ ከፓርቲዎች በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ማብራሪያ ይሰጣል።

ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :