አትሌቶች በኦሎምፒክና በአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉበትን አሰራር የሚቀይር ስርዓት ሊተገበር ነው
November 5, 2017 - አትሌቶች በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉበትን አሰራር የሚቀይር የዓለም የአትሌቶች ደረጃ ስርዓት ተግባራዊ ሊሆን ነው።
የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ስርዓቱን መተግበር የሚያስችለውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ከእንግሊዙ የቢዝነስ ተቋማት የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ኢሊት ኩባንያ ጋር ትናንት በፈረንሳይ ሞናኮ ተፈራርሟል።
ስርዓቱ እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ማህበሩ በየዓመቱ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች አትሌቶች ያስመዘገቡት ውጤት በመረጃ ቋት እንዲመዘገብ ያደርጋል።በዚሁ መሰረት አትሌቶች በዓመት ውስጥ ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት የሚሰጣቸው ነጥብ ተደምሮ በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።
የሚሰጣቸው ነጥብ ባስመዘገቡት ደረጃና የሚሳተፉባቸው ውድድሮች በማህበሩ በተሰጣቸው ደረጃና ባላቸው ፋይዳ ላይ እንደሚወሰን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል።
ይህ ስርዓት ማህበሩ በሚያካሂዳቸው ሁሉም የስፖርት አይነቶች የሚተገበር ነው።
ቀደም ሲል አትሌቶች በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉት በግል ምርጥ ሠዓት በማስመዝገብ የነበረ ሲሆን ይህ አሰራር ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የሚቆም ይሆናል።
የዓለም አትሌቶችን ደረጃ የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች፣ ማህበሩ ለሚያዘጋጃቸው ውድድሮች የሚሰጠው ነጥብና በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና መሳተፍ በሚቻልበት ሁኔታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
የአሰራር ስርዓቱ እ.ኤ.አ በ2019 በኳታር ዶሀና እ.ኤ.አ በ2020 በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተነግሯል።
የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በውድድር ስርዓቱ ላይ እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ እንደገለጹት በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ተግባራዊ የሚሆነው ስርዓት ዓለም አቀፉን የአትሌቲክስ የውድድር ስርዓት የሚለውጥ ነው።
"በስፖርቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አትሌቶች፣ የመገናኛ ብዙሃንና የስፖርቱ ቤተሰቦች ከአገር እስከ ዓለም አቀፍ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች የአትሌቶችን ደረጃ በግልጽ የሚለዩበት ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በዚህ ደረጃ መሰረት አትሌቶች በኦሎምፒክና በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የሚሳተፉበት መንገድ በግልጽ እንደሚለይ ገልጸዋል።
በጋራ መግባቢያ ሰነዱ አማካኝነት የአትሌቲክስ ታሪክና አትሌቶች ያገኟቸው ሽልማቶችና ያላቸውን የታሪክ ሰነድ በተሻለና በተቀናጀ መልኩ መያዝ ያስችላል የተባለ "የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ቅርስ" የተሰኘ የስራ ክፍል ተቋቁሟል።
የስራ ክፍሉ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ተጠቁሟል።
ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ