የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ከ45 ቀናት በኋላ እንዲካሄድ ተወሰነ
November 10, 2017 - ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን ወስኗል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬ ውሎው ምርጫው ከ45 ቀናት በኋላ ታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲደረግ ወስኗል።
የፌደሬሽ 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ፌደሬሽኑ ባዘጋጀው የጉባኤ መርሀ ግብር መሰረት ተጠባቂው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነገ ህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ከ3 ሰዓት ጀምሮ እንደሚያከናወን ያሳይ ነበር።
ሆኖም ግን በትናንትናው እለት በተካሄደው ጉባዔ ላይ ጠቅላላ ምርጫው በሌላ ጊዜ እንዲካሄድ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑም ይታወሳል።
የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን ምርጫው በአንድ ወር እንዲራዘም በይፋ መጠየቁ የሚያወስ ሲሆን፥ ሌሎች አንዳንድ ክልሎችም ምርጫው እንዲራዘም ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልፁ ነበር::
በዚህም መሰረት ምርጫው ከ45 ቀናት በኋላ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንዲካሄድ ነው ጉባዔው በዛሬው ውሎው የወሰነው።
በጉባዔው ስለ አስመራጭ ኮሚቴ እና የምርጫ ደንብ ምንም ውይይት ሳይደረግበት ቀርቷል።
ትናንት የተጀመረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የ2010 በጀት አመት እቅድ በማፅደቅ ተጠናቋል።
ኤፍ.ቢ.ሲ