በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ የተደረገው ማስተካከያ መድሃኒት አቅራቢ ደርጅትና የመንግስት ተቋማትን እያወዛገበ ነው

Birr-devaluationNovember 21, 2017 - በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ማስተካከያ መደረጉ መድሃኒቶችን ለማቅረብ ጨርታ ያሸነፉ የግል ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማትን በማወዛገብ ላይ ነው።

ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡት የኦፕቲማ ፋርማሲዩቲካል ትሬዲንግ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮናታን እስጢፋኖስ፥ የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም ከመደረጉ በፊት ለጨረታ ባስገቡት የገንዘብ መጠን የውል ስምምነት እንዲፈፀም በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ያነሳሉ።

ይሁንና የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ መዳከሙ እየታወቀ ከዚህ በፊት በነበረው ዋጋ የውል ስምምነት ልንፈፅም አይገባም የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።

ኬቲ ህይወት ሜዲካል የግል ማህበር ባለቤት አቶ ተገኝ ወርቁም በተመሳሳይ፥ ባሸነፍነው ጨረታ የውል ስምምነቱን እንዳንፈፅም አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታ ያገናዘበ አይደልም ሲሉ ያክላሉ።

የውል ስምምነቱን ብንፈፀም በዓለም ገቢያ ያለው የመድሃኒት ዋጋ በጨረታ ካቀረብነው ጋር የሚጣጣም አይደለም፤ ስምምነቱን ካልፈፀምን ደግሞ በጨረታው ለመሳተፍ ያስያዝነው ሁለት በመቶ የጠቅላላ ዋጋ በመንግስት ተቋማት ይወስድብናል ነው የሚሉት።

ጥያቄያቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን አቶ ተገኝ ገልፀዋል።

በጨረታ ላይ የሚቀርበው የገንዘብ መጠን የወቅቱን ገበያ መሰረት አድርገው ዋጋ የሚቀርብባቸው ናቸው።

ነገር ግን ከዋጋ ተለዋዋጭነት አንፃር እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ፥ ለማስተካከል የሚያስችል ምን ዓይነት አሰራር ይኖራል? ስንል ጥያቄያችንን ለፌዴራል የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ኤጀንሲ አቅርበናል።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰጠኝ ገላን፥ ከውጭ የሚመጡ እቃዎች ዓለምአቀፍ የገበያ ሁኔታዎችን መሰረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

በጨረታ አሸናፊው ድርጅት እና በመንግስት ተቋም መካከል የሚፈፀም የውል ስምምነት ደግሞ ለሶስት ወር ብቻ ግዴታ እንደተቀመጠለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በሂደት የሚያጋጥሙ ጉዳዮች ሲኖሩ በሁለቱ ተቋማት መካከል በሚፈፀም ስምምነት የሚወሰን ይሆናል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሰን በበኩላቸው፥ ለባለበጀት መስሪያ ቤቶች ሰኔ ላይ ከተመደበው በጀት ውጪ የብር የመግዛት አቅም መዳከምን ለማስተካከል የሚመደብ በጀት የለም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅም መዳከም በየጊዜው የሚደረግ ባይሆንም፥ መንግስት እንደዚህ ዓይነት ነገር በሚያጋጥምበት ጊዜ ችግሩን የሚፈታበት ሂደት በግዥ ስርዓቱ መመሪያ አለመኖሩ ክፍተት ነው።

ስለዚህ ቀጣይ በሚደረጉ የመንግስት የማሻሻያ ስራዎች መሰል ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ የሚመለከታቸው አካላት አስቀድመው ሊያጤኑት ይገባል።

ኤፍ.ቢ.ሲ


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :