በፊፋ ወርሃዊ ደረጃ ኢትዮጵያ 6 ደረጃዎችን አሻሻለች
November 24, 2017 - በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ወርሃዊው የሃገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 6 ደረጃዎችን አሻሽላለች።
ይህን ተከትሎም ከዓለም 145ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 44ኛ ደረጃን ይዛለች።
ኢትዮጵያ በወሩ 12 ደረጃዎችን ካሽቆለቆለችው ኢኳቶሪያል በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።የዓለም ቀዳሚ ደረጃዎችን ጀርመን በአንደኝነት ስትመራ ብራዚል እና ፖርቹጋል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ።
አርጀንቲና፣ ቤልጂየም፣ ስፔን፣ ፖላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ እና ቺሊ ደግም በቅደም ተከተል ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ሴኔጋል 23ኛ ደረጃን በመያዝ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ቱኒዚያ 27ኛ እና ግብፅ 31ኛ ደረጃን በመያዝ ከአፍሪካ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነዋል።
አንጉሊያ፣ ባህማስ፣ ኤርትራ፣ ጅብራልተር፣ ሶማሊያ እና ቶንጋ ደግሞ አሁንም ያለምንም ነጥብ በደረጃው ግርጌ ላይ ይገኛሉ።
በወሩ ሰሜን ኮሪያ 18፣ ሊባኖን 13 እንዲሁም ቡርኪናፋሶ እና ኢንዶኔዥያ 11 ደረጃዎችን በማሻሻል የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።
በአንጻሩ ኢኳዶር 22፣ ቻድ 19 እና እስራኤል 16 ደረጃዎችን አሽቆልቁለዋል።
ምንጭ፡ ኤፍ.ቢ.ሲ