ብሄራዊ ባንክ የወርቅ ዋጋ የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻ ዳግም ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ
December 2, 2017 - የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የወርቅ ዋጋ መውረድን ተከትሎ አንስቶ የነበረውን የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻ ዳግም ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
በክልሎች በተከፈቱ የወርቅ ግዥ ማዕከላት አቅራቢዎች የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንም ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ፤ ባንኩ ነጋዴዎቹን ለማበረታታት ወርቅ ለግብይት በቀረበበት ወር ያለውን የክፍያ ዋጋ መሰረት በማድረግ ሰፊ የመምረጫ ጊዜ ሲሰጥ እንደነበር አስታውሷል፡፡
ይህም የወርቁን ትክክለኛ ዋጋ የማያሳይና ባንኩን ለከፍተኛ ወጪ ሲዳርግ መቆየቱን አመልክቷል፡፡የዚህ ዓይነቱ አሰራር እንዲቀር መደረጉን ያወሳው የባንኩ መግለጫ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የወርቅ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ መንግስት አቅራቢዎችን በማበረታታት ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን አገራዊ ጥቅም ለማሳደግ መወሰኑን አውስቷል።
በዚህም ብሄራዊ ባንኩ አገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻውን እንደገና ተግባራዊ ማድረጉን ገልጿል፡፡
እንዲሁም ባንኩ የወርቅ ግዥ የሚፈጽመው በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ መሆኑን አውስቶ፤ አቅራቢዎች ወርቅ በብዛት እንዲያቀርቡ ለማበረታታት የፖሊሲ እርምጃ መውሰዱንም በመግለጫው አመልክቷል፡፡
በፖሊሲ ማሻሻያውም ቀደም ሲል ሲሰጥ ከነበረው ዋጋ ጭማሪ የአንድ በመቶ እና የሦስት በመቶን ወደ አምስት በመቶ ከፍ በማድረግ በእያንዳንዱ ግዢ ላይ ለነጋዴዎች ተጨማሪ ክፍያ እየተፈጸመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዝቅተኛ ወርቅ አቅራቢዎችን ለማበረታታት የቅበላ ጣራውን ከ150 ግራም ወደ 50 ግራም ዝቅ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡
ባንኩ ማበረታቻውን ከጥቅምት 4 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ ተግባር ላይ ማዋሉን በማስታወቅ ወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ባንኩ ባዘጋጀው ማበረታቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በባህላዊ መንገድ የሚመረተው ወርቅ ወደ ማዕከል ይቀርብ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፤ ግብይቱን በአንድ ማዕከል ማከናወኑ የአቅራቢዎቹን ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ በክልሎች የግዥ ማዕከላት ተከፍተው ግብይቱ እንዲከናወን መደረጉን አብራርቷል፡፡
የክልል የግዥ ማዕከላት መከፈት አቅራቢዎች ረጅም ጉዞ ሳያደርጉ፣ የትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎች ሳይኖርባቸው ወርቃቸውን እንዲሸጡ በመደረጉ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት መቻላቸውን ጠቁሟል።
ኢዜአ