የንግድ ሕግ የሚያሻሽል አዲስ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ
December 3, 2017 - ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘውን የንግድ ሕግ የሚያሻሽል አዲስ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በተጨማሪም ከ1954 ዓ.ም. ጀምሮ በተግባር ላይ የቆየውንና ተሞክሮ በተደጋጋሚ ውድቅ ተደርጎ የነበረው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉንም ለማሻሻል፣ ድጋሚ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ መቅረቡንም ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ረቡዕ ኅዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት የመሥሪያ ቤታቸውን የሩብ ዓመት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ሕጎች ላለፉት አምስት አሠርት ዓመታት ሳይሻሻሉ ከቀሩት አምስት በላይ ሕጎች መሠረታዊ (ኮዶች) የሚካተቱ ሲሆን፣ ለምን ይህን ያህል ጊዜ እንደቆዩ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች ውስጥ ይገኙበታል፡፡
ለጥያቄዎቹ ማብራርያ የሰጡት ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ እነዚህ ሕጎችን ለመከለስ ወይም ለማሻሻል እንደ መደበኛ አዋጆች ቀላል ባለመሆናቸውና የመንግሥት ውሳኔና የፖሊሲ ለውጥ የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
በሁለቱም ሕጎች ዙሪያ የተዘጋጁ ረቂቅ ማሻሻያዎችን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደጋጋሚ ውይይትና የማዳበሪያ ሐሳቦች ተደርጎባቸው፣ ባለፈው ሳምንት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላካቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
አክለውም የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የቀረቡለትን ረቂቆች መርምሮ ‹‹በእኛ በኩል የጎደለ ነገር አለመኖሩን ካረጋገጠ በቅርቡ በምክር ቤቱ (ተወካዮች ምክር ቤት) ቀርበው በእጃችሁ እንደሚደርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› በማለት አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡
ነገር ግን በሁለቱም ረቂቅ ማሻሻያ ሕጎች ስለተካተቱ ዝርዝር ሕጎችና ማሻሻያዎች ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ አገዛዝ ዘመናት ከ1947 እስከ 1957 ዓ.ም. ድረስ ስድስት ሕጎች የወጡ ሲሆን፣ ከወንጀለኛ ሕጉ በስተቀር አምስቱም እስከ ዛሬ ድረስ አልተሻሻሉም፡፡
በ1997 ዓ.ም. የወንጀል ሕጉ በቀድሞ አጠራሩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሻሻሉ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የወንጀል ሕጉ ብቻውን ያለወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሻሻሉ ጥያቄ ሲነሳበት ቆይቷል፡፡
የሕግ ባለሙያዎች ቢያንስ ሁለቱ ሕጎች ተያያዥ እንደ መሆናቸው መጠን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ባይሆን እንኳ ብዙም ሳይቆይ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሊሻሻል ይገባው እንደነበር ይከራከራሉ፡፡ ቀድሞ የተሻሻለው የወንጀል ሕጉ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ ዘመኑ የፈጠራቸውን መሻሻሎች፣ ነባራዊ ሁኔታዎችና ተያያዥ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ታሳቢ አድርጎ መሻሻሉ ይነገራል፡፡ ለአብነትም ያህል በቀድሞ ሕግ ያልተካቱን እንደ የኮምፒዩተር ነክ ወንጀሎችን፣ የአውሮፕላን ጠለፋን፣ የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርንና የአካባቢ ብክለትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማካተት የተሰናዳ ነው፡፡
ምንጭ: ሪፓርተር