የኢትዮጵያ ከ17 በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር አንድ እኩል በሆነ ውጤት ተለያየ
December 5, 2017 - ኡራጓይ በ2018 ለምታስተናግደው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ከ17 በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይይጄሪያ አቻው ጋር ባደረገው የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ አንድ እኩል ወጥቷል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ናይጄሪያ በ22ኛው ደቂቃ በፕሪሺየስ ቪንሰንት ጎል መሪ የነበረች ቢሆንም በ63ኛው ደቂቃ ታሪኳ ደቢሶ ለቡድኗ የአቻነቷን ጎል አስቆጥራለች።
ናይጄሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እድሏን ስታሰፋ የኢትዮጵያ ከ17 በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሜዳ እድሉን ሳይጠቀም ቀርቷል።
የማጣሪያው የመልስ ጨዋታ ታህሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በናይጄሪያ ቤኒን ከተማ በሚገኘው ሳሙኤል ኦግቤዲያ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።በድምር ውጤት ያሸነፈው ቡድን በቀጣዩ ዙር ከካሜሮንና ከአልጄሪያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር የካቲት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።
ከትናንት በስቲያ የካሜሮን ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ የአልጄሪያ አቻውን አራት ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉን ማስፋት ችሏል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ከኬንያ አቻው ጋር እንዲጫወት ተመድቦ የነበረ ቢሆንም የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን በማግለሉ ከናይጄሪያ ጋር እንዲጫወት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) መወሰኑ የሚታወስ ነው።
16 ቡድኖች በሚሳተፉበት ውድድር ሶስት የአፍሪካ አገራት የመሳተፍ ኮታ አላቸው።
የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ፊፋ ዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሲሆን፣ በቀጣይ ለስድስተኛ ጊዜ በዑራጓይ አዘጋጅነት ከኅዳር 11 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ይከናወናል።
ምንጭ፡ ኢ.ዜ.አ