ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች በየወሩ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ውጭ እየላከች ነው
December 8, 2017 - ከአምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በየወሩ አስር ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ወደ ውጭ እየተላኩ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ። ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የላኩት በመንግስት የተገነቡት የሐዋሳና የቦሌ ለሚ ሲሆኑ በግል ባለኃብቶች የተገነቡት የምስራቅ፣ ጆርጅ ሹ እና ቦግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው።ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርና ምርቶች ሲሆኑ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ድርሻ ገና በነጠላ አሀዝ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም ከአጠቃላይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የኢንዱስትሪውን ድርሻ 25 በመቶ በማድረስ ወደ ውጭ አገራት ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ 50 በመቶ ያህሉን ከማምረቻ ኢንዱስትሪው የመላክ እቅድ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለተቀመጠው እቅድ ስኬት ተስፋ እንደተጣለባቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት ለዚህ ግብ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱትና ወደ ምርት ከተሸጋገሩት አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ ከሁለት ወር በኋላ የመቐሌና ኮምቦልቻ ፓርኮች ወደ ምርት ይገባሉ።ወደ ምርት የተሸጋገሩት አምስቱ ፓርኮች በጥቅምት ወር አስር ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ወደ ውጭ መላካቸውንም ገልጸዋል።
በማምረት ላይ ያሉት እነዚህ አምስት ፓርኮች ለ40 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ዶክተር በላቸው ተናግረዋል።በሶስተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በየዓመቱ ለ200 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው።ባለፈው 2009 በጀት ዓመት አገሪቱ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አራት ቢሊዮን ዶላር መሳብ መቻሏንና አብዛኛዎቹ ባለሐብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በወጪና ገቢ የትራንስፖርት አገልግሎት ፍጥነት ፣ ዋጋና የማጓጓዝ መጠን እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ለኢንቨስትመንቱ ፍሰት ማደግ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ ያሳደሩትን ጫና መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።
በመሆኑም የባቡር መሰረተ ልማትና ሌሎች የማዳረሻ መንገዶች ግንባታና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ለመፍታት የዶላር የምንዛሪ ዋጋ ላይ ማስተካክያ እርምጃዎች ከተወሰዱት ዘላቂ መፍትሄዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ተመጋጋቢ የሆኑ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በመንግስታቱ ድርጅት መሸለሟ አይዘነጋም።
ምንጭ፡ ኢ.ዜ.አ