የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኑን ገለጸ
December 18, 2017 - የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የምርጫ ህግ ባለመኖሩ ምክንያት መቸገሩን ገለጸ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚመሩ ፕሬዚዳንትና ስራ አስፍጻሚ ምርጫ ጉዳይ የሚከተታል አስመራጭ ኮሚቴና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ መምረጡ የሚታወስ ነው።
ይህ አስመራጭ ኮሚቴ እየሰራቸው ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም አስመራጭ ኮሚቴው ምርጫን በተመከለተ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በኩል የተቀመጠ የምርጫ ህግ ባለመኖሩ ስራውን ለመስራት መቸገሩን ገልጿል።
አስመራጭ ኮሚቴው የአለም አቀፉን እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ህግን ተከትሎ እንደ ሀገሪቱ ነበራዊ ሁኔታ ህጉ ባለመቀመጡ አያሰራንም በሚል የአንዳንድ አባላት ጥያቄ ተግባራዊ ለማድረግ ተቸግሯል።
ይህ በመሆኑም አንዳንዴ የፊፋን ህግ ተከትሎ ይሰራል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የፊፋን በጣሰ መልኩ በአስመራጭ ኮሚቴው በአብላጫ ድምጽ እንዲወሰኑ የተደረጉ ጉዳዮች እንዳሉ የተነገረው።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጉዳዮችን እንዲጣሩለት እየጠየቀ የወሰናቸው ጉዳዮች እንዳሉ ነው የገለጸው። በዚህ መልኩ እየሰራ ያለው አስመራጭ ኮሚቴ የአንዳንድ እጩ ተወዳዳሪዎች ጉዳይ ላይም በምን መልኩ መስራት እንዳለባቸው በመቸገራችው ምክንያት በድምጽ ብልጫ እና ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በተገኙ መረጃዎች መሰረት ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸዋል።
የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት በሁለት ጎራ እንዲከፈሉ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል አንድ አባል ከዚህ በፊት ምርጫ ላይ ተካፍሎ ከሆነ ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፍ አይችልም የሚለው የፊፋ ህግ ነው።
በዚህ የምርጫ ህግ መሰረት ደግሞ በ2006 የፌዴሽኑ ምርጫ ላይ አስመራጭ ኮሚቴ ሆነው የሰሩና አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡ አባል ጉዳይ አንዱ የውዝግብ አጅንዳ ፈጥሮ እንደነበር ነው የተገለጸው።
በመጨረሻም የፊፋ ህግ በሚጣረስ መልኩ አስመራጭ ኮሚቴው በድምጽ ብልጫ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ምንጭ: ኢ.ዜ.አ