የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከስራቸዉ ለቀቁ
December 26, 2017 - የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስገቡት የስራ መልቀቂያ ተቀባይነት አገኘ። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን በሻህ የአሰልጣኙ የስራ መልቀቂያ በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት ማግኘቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል።አሰልጣኝ አሸናፊ በ100 ሺህ ብር ወርኃዊ ደመወዝ ዋልያዎቹን ለማሰልጠን ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር የሁለት ዓመት ኮንትራት የተሰጣቸው።
ኮንትራቱም ከመጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ የነበረ ሲሆን፥ በቆይታቸው ዋልያዎቹን ካሜሮን ለምታስተናግደው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታ ተጥሎባቸው እንደበረ ይታወሳል። አሰልጣኝ አሸናፊ በወቅቱ በሰጡት መግለጫም፥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድንን በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሩብ ፍጻሜ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልፀው ነበር።
"ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ብቻ አይደለም ለቻን ውድድር ማሳለፍ ካልቻልኩ ሁለት ዓመት አልጠብቅም፤ በራሴ ፍቃድ እለቃለሁ" ማለታቸውም አይዘነጋም።አሰልጣኙ 2009 ዓ.ም ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ከመጡ ወዲህ ግን ብሄራዊ ቡድኑ ማሸነፍ የቻለው ደቡብ ሱዳን እና ጅቡቲን ብቻ ነው።
በብሄራዊ ቡድኑ ቆይታቸው ስኬታማ መሆን ያልቻሉት አሰልጣኝ አሸናፊ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስገብተውት የነበረው የስራ መልቀቂያ በዛሬው እለት ተቀባይነት አግኝቶላቸው ከዋልያዎቹ ጋር ተለያይተዋል።አሰልጣኝ አሸናፊ በቀጣይም ኢትዮ-ኤሌክትሪክን እንደሚያሰለጥኑ ተሰምቷል።
በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ባለፈው ሳምንት ከስመምነት ደርሰዋል። ይህንን ተክተሎም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፤ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩን ተክተው በ2ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ቡድኑን እንደሚመሩ ይጠበቃል።
ምንጭ:- ኤፍ.ቢ.ሲ