ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሠራተኞች አድማ ሥራ አቆመ
January 7, 2018 - ደርባ ሚድሮክ ከታኅሳስ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሠራተኞች አድማ ምክንያት ሥራ አቆመ፡፡ የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ እንደገለጹት፣ ስድስት ያህል ዓላማቸው ግልጽ ያልሆነ ሠራተኞች ለሌሎች ሠራተኞች ማስፈራርያ በመላክ ሥራ እንዲቆም አድርገዋል፡፡
‹‹የሲሚንቶ ምርት ቆሟል፡፡ በአጠቃላይ ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አቁሟል፡፡ በክምችት ያለውንም ምርት ለገበያ ማቅረብ አልተቻለም፤›› ሲሉ አቶ ኃይሌ ገልጸው፣ ‹‹ችግሩን ከወረዳውም ሆነ ከዞኑ ጋር በመነጋገር ለመፍታት ቢሞከርም ሊሳካ ግን አልተቻለም፤›› ሲሉ ደርባ ሚድሮክ የገጠመውን ችግር አስረድተዋል፡፡
የሥራ ማቆም አድማ ከመመታቱ በፊት የግዙፉ ደርባ ሚድሮክ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጠይቀው ነበር፡፡ በተለይ መንግሥት ብር ከዶላር ጋር ያለውን ምጣኔ በ15 በመቶ እንዲቀንስ በማድረጉ፣ ሠራተኞች 15 በመቶ ደመወዝ እንዲጨመርላቸው መጠየቃቸውን አቶ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማኔጅመንት ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር ከመከረ በኋላ ስምምነት ላይ በመድረሱ፣ 25 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ደርባ ሚድሮክ በሠራተኞች ከተጠየቀው 15 በመቶ ጭማሪ አሥር በመቶ ያህል በመጨመር 25 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ አድርጓል፤›› ሲሉ አቶ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡
ይህ ጥያቄ ከተፈታ በኋላ ደግሞ የመዋቅር ለውጥ እንዲደረግ ከሠራተኞች ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ይህን የመዋቅር ጥያቄ ለማየት የሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰጥና ኮንሰልታንት ተቀጥሮ እንዲሠራ ብንስማማም፣ ዓላማቸው ግልጽ ያልሆኑ ሠራተኞች በተለያዩ ክፍሎች ለሚሠሩ ሠራተኛው ማስፈራርያ በመላክ የሥራ ማቆም አድማ እንዲመታ አድርገዋል፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የደርባ ሚድሮክ ሠራተኞች ማኅበርም ተሰሚነት እንዳጣ አቶ ኃይሌ አስታውቀዋል፡፡
ችግሩን የኦሮሚያ ክልል መዋቅሮች በተለይም ወረዳውና ዞኑ ሊፈቱት ባለመቻሉ፣ ‹‹በዚህ ሳምንት ጉዳዩን ወደ ፌዴራል መንግሥት እንወስደዋለን፤›› ሲሉ አቶ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡
ደርባ ሚድሮክ 740 ቋሚ ሠራተኞችና 460 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት ደርባ ሲሚንቶ ወደ ገበያ እየቀረበ አለመሆኑ ታውቋል፡፡
ምንጭ: ሪፖርተር