የኢትዮጵያ አየር መንገድ 6.87 ቢሊዮን ብር አተረፈ
August 14, 2018 - የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6.8 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የድርጅቱን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ዓርብ ነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ አየር መንገዱ 10.6 ሚሊዮን መንገደኞችና 400,339 ቶን ጭነት እንዳጓጓዘ ተናግረዋል፡፡ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የመንገደኞች ቁጥር በ21 በመቶ፣ የጭነት መጠን ደግሞ በ18 በመቶ እንዳደገ አስረድተዋል፡፡
የአየር መንገዱ ገቢ በ43 በመቶ ዕድገት በማሳየት 89.1 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ተገልጿል፡፡ አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ ስምንት ዓለም አቀፍና ሁለት የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እንደከፈተ ተነግሯል፡፡ ኩባንያው 14 አዲስ አውሮፕላኖች የተረከበ መሆኑን፣ በአዲሱ ዓመት 20 አዲስ አውሮፕላኖች እንደሚያስገባ ተገልጿል፡፡
‹‹አየር መንገዱ ይህን ውጤት ሊያስመዘግብ የቻለው የኩባንያው ማኔጅመንትና 13,000 ሠራተኞች ጠንክረው በመሥራታቸው ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ ወቅቱም የዓለም አየር መንገዶች በተለያዩ ችግሮች የተፈተኑበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከተጠበቀው በላይ መናር አየር መንገዶችን እየተፈታተነ ያለ ችግር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ከ30 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተገልጿል፡፡ ‹‹እኛ ስናቅድ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 56 ዶላር ይሆናል ብለን ነበር የያዝነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በጣም ንሮ ከ67 እስከ 70 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡ ነዳጅ የአንድ አየር መንገድን አጠቃላይ ወጪ ከ30 እስከ 40 በመቶ ይይዛል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አጠቃላይ ወጪ 40 በመቶ የነዳጅ ወጪ በመሆኑ እየናረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሮብናል፤›› ብለዋል፡፡ በማንኛውም ወቅት አፍሪካ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ከተቀረው ዓለም አማካይ የነዳጅ ዋጋ በ30 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተገልጿል፡፡
Source: Reporter