ኢትዮ ቴሌኮም በስልክ አገልግሎት ላይ የታሪፍ ቅናሽ አደረገ
August 22, 2018 - ኢትዮ ቴሌኮም ዛሬ በሰጠው መግለጫ፥ ተቋሙ በሞባይል ስልክ እና በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል።
በዚህ መሰረት የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የ43 በመቶ፣ የስልክ ድምፅ ላይ የ40 ከመቶ እንዲሁም አጭር የሞባይል የፅሁፍ መልዕክት ላይ የ43 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን ገልጿል።
የታሪፍ ቅናሹ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ነው የገለጸው።
የታሪፍ ቅናሹን ተከትሎም በደቂቃ 83 ሳንቲም የነበረው የሞባይል ስልክ ጥሪ አገልግሎት ወደ 50 ሳንቲም ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
ከዚህ ባለፈም ቀደም ሲል በሜጋ ባይት 35 ሳንቲም የነበረው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት 43 በመቶ ቅናሽ ተደርጎበት በሜጋ ባይት ወደ 23 ሳንቲም ዝቅ ብሏል።
በአጠቃላይ በሞባይል ኢንተርኔት ፓኬጆች ላይ ደግሞ ከ33 እስከ 44 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል።
በሞባይል እና መደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይም እስከ 54 በመቶ ቅናሽ መደረጉም ተገልጿል።
የብሮድባንድ ሲም ካርድ ሽያጭ ለጊዜው የተቋረጠ ሲሆን፥ በቀጣይ መስፈርቱን ከሚያሟሉ ባንኮች፣ ሆቴሎች እና ሱፐርማርኬቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር የብሮድባንድ ሲም ካርድ ሽያጭ እንዲያከናወን ይደረጋልም ነው ያለው።
Source: FBC