አለም አቀፍ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ስራ እንዲሰማሩ ተወሰነ
September 4, 2018 - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠንና ኢንቨስትመንትን እንዲሁም የውጭ ንግድ አፈፃፀምን በበቂ መጠን ለማሳደግ የሚያግዝ የፖሊሲ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ የተላለፈው ውሳኔ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር ከሀገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች በሽርክና መስራት የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል።
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የውጭ ንግድ አፈፃፀምን በበቂ መጠን ለማሳደግ የሎጂስቲክስ እና የጉምሩክ አሰራሮችን ማሻሻል እንደሚገባ የተገለፀ ቢሆንም እስካሁን በዘርፉ ይህ ነው የሚባል ጉልህ መሻሻል አልታየም ብሏል ቦርዱ በመግለጫው።
በአጠቃላይ ዘርፉ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅ ብዙ ርቀት መጓዝ የሚኖርበት ሲሆን፥ ለዚህም እንደማሳያ የሚሆነው የሀገሪቱ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪና የጉምሩክ ስርዓት ከአለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ አፈፃፀም ላይ መገኘቱ ነው።
ይህንንም ለማስተካከልና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተያዙ እቅዶችን ወደ መሬት ለማውረድ የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ፀድቋል።
Source: FBC