የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በአዲስ ስያሜ ሊደራጅ ነው

METEC-reorgOctober 15, 2018 - የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወታደራዊ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር በማስረከብ በአዲስ ስያሜ ሊደራጅ ነው።

ከተቋቋመ ጀምሮ በጥቂት ጊዜ በርካታ የመንግስት ፕሮጀክቶችን እንዲይዝ ተደርጎ የነበረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከብቃት፣ እጦትና ከብክነት ጋር ተያያዘ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል።

እጁ ላይ የነበሩ በርካታ የስኳር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ አቅቶት ፕሮጀክቶቹን ሲቀማ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሃይድሮ መካኒካል ስራዎችን ወስዶ መስራት ባለመቻሉም ቢሊየን ብሮች እንደባከኑ ተሰምቷል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የኮርፖሬሽኑን አመራሮች ከመቀየር አንስቶ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰድበት እያደረገ ነው።

የኮርፖሬሽኑ የኮመርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልዓዚዝ መሀመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ አሁን በመንግስት የተወሰደው እርምጃ የኮርፖሬሽኑን አደረጃጀት ማስተካከል ነው።

ይህም በሜቴክ ስር ወታደራዊ ምርቶችን ሲያመርቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር በመስጠት ቀሪዎችን በስሩ የሚያስቀጥል መሆኑንም ይናገራሉ።

በዚህ መሰረት ሜቴክ አዲሱን ስያሜ ይዞ የሲቪልና የንግድ ምርቶችን ብቻ የሚያመርት ሲሆን፥ የብሄራዊ ብረታ ብረት ምህንድስና ኮርፖሬሽን የሚል አዲስ ስያሜ ሊሰጠው እንደታሰበም ተናግረዋል።

ለዚህ አዲስ አደረጃጀት ረቂቅ ደንብ የተዘጋጀ ሲሆን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸቀደ በኋላ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

Source: FBC


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :