የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን - በቅሎን ሲያታልሏት አስረዝመው አሰሯት

በህይወት ዳምጤ

እግር ከወርች የታሰረው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን ምን አይነት ማሻሻያ ያስፈልገዋል?

Ethiopian-MediaApril 30, 2019 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን ታሪክ ጅማሮ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ምኅዳሩን በተቀላቀለችው አእምሮ ጋዜጣ መበሰሩን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ታዲያ አንድ ምዕተ ዓመትን የተሻገረው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ምን ያህል ርቀትን ተጓዘ ለሚለው በመንግስት የበላይነት ተጠፍንጎ ስለመጓዙና እስካሁንም እንደሚገኝ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ መንግስት ጀምሮ እስከ ዛሬው መንግስት ድረስ የመገናኛ ብዙኸን ነፃነት ከገዢ መንግስታት መዳፍ መላቀቅ አለመቻሉንም የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ከሳምንታት በፊት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ (ECA) በሲዊድን ኤምባሲ አዘጋጅነት በመገናኛ ብዙኸን ዙሪያ የመከረ ጉባኤ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል፡፡ በዚህ መድረክ ንግግር ካደረጉት ሙህራን ውስጥ አንዱ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የመገናኛ ብዙኸን ህግ ሙህር ፕሮፌሰር ዘካሪስ ቀና፤ የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙኸን “የመንግስት መሳሪያና ወገንተኛ” ነው ሲሉ ይገልፁታል፡፡ ታዲያ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኸን በልቡና እንደሚታሰበው አራተኛ መንግስት ሆኖ እንዳይገዳደር፣ ለህዝቡና ለእውነት እንዳይቆም እንዲሁም ሚናውን እንዳይወጣ እግሩን ለምንና እንዴት ታሰረ? ለእድገቱ መሰናክሉስ ምንድ ነው?

መሰናክል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን ለምን እድገት የለሽ ሆነ ለሚለው ነፃነቱ በመንግስት መነፈጉ፤ በስመ ህግ መታሰሩ እንዲሁም ከገዥ መንግስታት የሚደርሱ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ጫናዎች ከባድ መሆን በቀዳሚ ምክንያትነት ይነሳሉ፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ብሩህ ይሁንበላይ መገናኛ ብዙኸን እንዳያድጉ ትልቅ እንቅፋት የሆነባቸው የፕሮፌሽናሊዝም ወይም የሙያ እጦት ነው ባይ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ከጋዜጠኛነት ይልቅ ፖለቲከኛነቱ እያመዘነበት ነው፤ ይህም ሚዛናዊነትን በማዛባት ሙያው ላይ ጥላውን እንዲያጠላ አድርጓል የሚል እምነት አለው፡፡

የቀድሞው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ስራ አስኪያጅና የመገናኛ ብዙኸንና የፖለቲካ ተንታኙ መሀመድ አዴሞም ከብሩህ ይሁንበላይ ጋር ይስማማል፡፡ ጋዜጠኛው ከጋዜጠኝነት ይልቅ ፖለቲከኛነቱ አድልቶበት ወገንተኛ አስተሳሰቡን በተከበረው የጋዜጠኝነት ሙያ እያንፀባረቀው ነው ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ለመገናኛ ብዙኸን እድገት መሰናከል ሆኗል ሲል ጫናውን ይገልፃል፡፡

የመረጃ ነፃነትና የመንግስት ተጠያቂነት ባህል የመገናኛ ብዙኸኑ እምርታ እንዳያሳዩና የሚታለመውን ሚና እንዳይወጡ እንቅፋት ስለመሆኑም ይነሳል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የመረጃ ነፃነትን የሚደነግግ አዋጅ እና በሁሉም የመንግስት ተቋማት መረጃን እንዲሰጡ የተቋቋሙ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ቢሮዎች እስከ ባለሞያዎቻቸው ቢኖሩም፡፡

የመገናኛ ብዙኸን አዝጋሚ የእድገት ችግር ወደ መንግስት ብቻ ጣት መቀሰር እንደማይገባ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እራሱ ብዙኸን መገናኛው ከሙያ አለመብሰልና ከአቅም ውስንነት (የገንዘብና የፕሮፌስናሊዝም) አንዳልተላቀቀ በመጠቆም ለዘርፉ ስጋት ነው ይባላል፡፡ መፍትሄውም ለመንግስትና ለብዙኸን መገናኛዎች ብቻ የተተወ አይደለም፤ የሲቪክ ማህበራት፣ የህዝቡ፤ የሁሉም ነው፡፡

ያቆጠቆጠው ብሄርተኛ መገናኛ ብዙኸን

ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በሀገራዊ ተቃውሞ የተናጠችው ኢትዮጵያ፤ ይህ ትርምስ በርካታ ነባራዊ ሁኖታዎቿን እንዳይመለሱ አድርጎ ቀይሮባታል፡፡ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኸኗን ብንመለከት፤ ዋልታ ረገጥና ወገንተኝነት እየተስተዋለ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ የአንድ ምዕተ ዓመት እድሜን ላልተሻገረው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን፤ ሀገሪቱን ከመሩት መንግስታት ጀምሮ ስራው ላይ እስካለው ባለሞያ ድረስ እንዳይሰራ ሆኖ እግሩ ተተብትቧል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ከጋዜጠኝነት መርሆዎች እውነታን መናገር፣ ሚዛናዊነትና ገለልተኝነት ያፈነገጡ ዜናዎች ሆኑ ፕሮግራሞች ለአድማጭ ለተመልካችና ለአንባቢያን ተደራሽ ሲሆኑ እየታዘብንም ነው፡፡ መገናኛ ብዙኸን ቀድሞውኑ ሲመሰረቱ ለማህበረሰቡ የሚሰጡት ግልጋሎትና የሚጫወቱት ሚና እሙን ነው፡፡ ለአብነት ያህል አስተማሪና አዝናኝ መረጃዎችን ከማድረስ ባሻገር በአንድ ማህበረሰብ ግንባታም ሆነ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ሚናቸው ወደር የለሽ ስለመሆኑ የዘርፉ ሙህራን ይናገራሉ፡፡ ለአብነት ያህል መገናኛ ብዙኸን የጋራ ማህበራዊ እሴቶችን በማጉላት ለአንድነት ያላቸው ሚና እንደ ኃላፊነታቸው ተሸክመውታልም፡፡ ሆኖም የሀገሪቱ የመገናኛ ቡዙኸን አሁናዊና ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የራቀ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ያስችላል፡፡ በተለይም የክልልና በዚህ አንድ ዓመት በሳተላይትና በህትመት ብቅ ያሉት የንግድ ወይም የግል መገናኛ ብዙኸንን በናሙናነት ማንሳት ይቻላል፡፡

የዘርፉ ሙህራንና ባለሞያዎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከፈቱና በየክልሎቹ ያሉ መገናኛ ብዙኸን ሚናቸውን የዘነጉ፤ ለማህበረሰቡ መስጠት ያለባቸውን ግልጋሎትና ፋይዳ የሸሹ፤ ህዝብን ከህዝብ የሚያነታርኩ እንዲሁም ወግነንለታል ለሚሉት ቡድንና ብሄር ጥቅም ያሉትን ሁሉ ለማስፈፀም አንድነትን ስለመሸርሸራቸው ይመሰክራሉ፡፡

ወትሮም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን በአመዛኙ አመሰራረታቸው ለፖለቲካ ድርጅት አፈ ቀላጤ ለመሆን ሲሆን፤ አልፎ አልፎም (በተለይም በ1990ዎቹ) መንግስትን በጭፍን ለመቃወም ሲባል ይመሰረታሉ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ተቃርኖን በጥላቻ ለማንፀባረቅና ቆመንለታል ለሚሉት ብሄር ብቻ ለመወገን ዓላማን ሰንቀው መስራትን ተያይዘውለታል፡፡

በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኸን የግልና የመንግስት ተብሎ መከፈል ያለና ተለመደ ቢሆንም አሁን አሁን የብሄር መገናኛ ብዙኸን እያቆጠቆጠ ነው፡፡ አንድን ብሄር እወክላለሁ ብሎ የሚቋቋም መገናኛ ብዙኸን በአግባቡና ዲሞክራሲዊ በሆነ መንገድ ቢወክል መልካም የነበር ቢሆንም፤ ሆኖም እውነታው ከዚህ የራቀ ስለመሆኑ መታዘብ ይቻላል፡፡ አንዱን ለመጥቀም ሌላውን ማጣጣልና መጉዳት እየተስተዋለ ነው፡፡ ጎሰኛ መገናኛ ብዙኸን በመርህ የሚመራው ጋዜጠኝነት ከአቀንቃኝነት ጋር መቀላቀሉም አዲስ ሁነት ሆኗል፡፡

እናም ብሄርን መሰረት ደረጉት መገናኛ ብዙኸኑ በጋዜጠኝነት መርህና በኤዲቶሪያል ፖሊሲ አለመመራታቸው፤ የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆኑ አድረጓቸዋል፤ ስሜታዊና ብሶት ቀስቃሽም ሆነዋል፤ ከአንዱ ወገን የሚሰነዘርን ትችት አፃፋ ለመመለስ ይሯሯጣሉ፡፡
መገናኛ ብዙኸን “በሁለት የተሳለ ሰይፍ ነው” ይላሉ ባለሞያዎች የሚያስከትለውን ውጤት በማየት፡፡ እናም ለአድማጭ፣ ለተመልካችና ለአንባቢያን የሚደርሱ ውጤቶች ጉዳት እንዳደርሱ ወይም ጉዳቱን ለመቀነስ ጥንቃቄ ማድረግ አንዱ የጋዜጠኝነት መርሆ ነው፡፡ ሆኖም የሀገሪቱ ብዙኸን መገናኛዎች ወገንተኛ መሆን እና በተለይም ለአንደኛው ብሄር ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ሌላኛውን መንቆር እየተላመዱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በብዙኸን መገናኛዎች የሚሰራጩ መሰናዶዎችን ናሙና በመውሰድ የሀገሪቱን የብሮድካስት ህግና ሌሎች የሚዲያ ህጎችን መሰረት በማድረግ የቁጥጥር ስራ ያከናውናል፡፡  ሆኖም  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የክልልና አንዳንድ የንግድ መገናና ብዙኸን ማህበራዊ እሴቶችንና አንድነትን ከማጉላት ይልቅ ፀብ አጫሪነት ሲስተዋልባቸው፤ ቆመንለታል ለሚሉት ወገን አሊያም ብሄር ጥቅምና ፍላጎት ሲሉ ተንኳሽ ሲሆኑ ብሮድካስት ባለስልጣን ጆሮ ዳባ ልበስ  ስለማለቱ በዝምታው መሀል ማጤን አይከብድም፡፡

ለዘመናት አጨብጫቢ ሆነው የቀሩት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን አሁን ላይ ቋንቋና ዘርን ማዕከል አድርገው መቋቋምና መስራት ከኢንዱስትሪው ህልውና አልፎም ሀገራዊ አንድነትና ሠላም ላይ ስጋትን ደንቅረዋል፡፡

አዲስ እረተሻሻሉ ያሉ ህጎች እነዚህን ዋልታ ረገጥ መገናኛ ብዙኸን ምን አልባትም በረቂቅ ላይ የሚገው የፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጁ አደብ ሊያስይዛቸው ይችላል፡፡ የዘርፉ ባለሞያዎች ለችግሩ ፍቱን መድሀኒቱ ግን ተከሻ ላይ የወደቀን ማህበራዊ ኃላፊነትና ሙያዊ ስነ ምግባርን ማክበር ነው ይላሉ፡፡

መንግስት ለረጅም ዓመታት የመገናኛ ብዙኸን ገዥ ወይም አስተዳዳሪ ነው፡፡ በተለይ አሁን ላይ ከዚህ ቀደሙ እውነታ ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን የተሻለ ነፃነት አግኝተዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከሰሞኑንም ጆርናሊስትስ ዊዝ አውት ቦርደር የተሰኘው ተቋም ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኸን ነፃነት ጥሩ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጿል፡፡ እናም አሁን ላይ መገናኛ ብዙኸንን “ማን ያስተዳድረው?” ለሚለው የውዝግብ ጥያቄ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዘካሪስ “የጋራ አስተዳደር” ምክረ ሀሳብን አቅርበዋል፡፡ መንግስትም የለመደውን እጁን መሰብሰብ ስለማይችል፤ መገናኛ ብዙኸንም በእግሩ አለመቆሙ የጋራ አስተዳደር እንዲመሰርቱ የግድ ይላቸዋል ይላሉ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡፡

ምን አይነት ማሻሻያ?

ለዘመናት በችግሮች የተተበተውን እና የአራተኛ መንግስት ሚናውን ስለመፈጠሩ የዘነጋው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኸን ምን አይነት ማሻሻያ ያስፈልገዋል?  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የመገናኛ ብዙኸን ህግ ሙህሩ ፕሮፌሰር ዘካሪስ ቀና ለሁሉም ተፈፃሚ የሚሆን የህግ ማዕቀፍ እና ነፃ ፍ/ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ይመክራሉ፡፡ መንግስትም ከመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ላይ እጁን መሰብሰብ አለበት የሚሉት ፕሮፌሰር ዘካሪያስ የመገናኛ ብዙኸን  የሀሳቦች ነፃ ገበያ መሆን እንዳለባቸውም አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ለማህበረሰቡና ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ እንደሚሆኑ፣ በተቃራኒው ከዚህ ከራቁ መዳረሻችንም የማይተነበይ እንደሚሆን ያክለሉ፡፡

መገናኛ ብዙኸኑን በህግ ስም ሲያቀጭጭና እራሱን ሴንሰር እንዲደርግ ሲያስገድዱ የነበሩ ህጎችን ማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነም የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጁ ብሩህ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ይቁም፤ የመገናኛ ብዙኸን ህግ ለመገናኛ ብዙኸኑ ነፃነት ይሰጣቸው፤ በአንድ ህግ ፈቅዶ በሌላኛው ማሰር የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙኸን መገለጫ በቅሎን ሲያታልሏት አስረዝመው አሰሯት ዓይነት ለበጣ አድርጎታል ይላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየውን መገናኛ ብዙኸን የተሰጣቸውን ነፃነት መሸከም ያለመቻልና ከነፃነት ጋር ያለውን ኃላፊነት የመዘንጋት ጥንውት መሰመር አለበት፡፡ ስለሆነም ህግን ተከትሎ በአግባቡ መስራት ለመገናኛ ብዙሃን ሀ፣ ሁ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ሙህራን ያስታውሳሉ፡፡ በመደበኛ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሳይቀር እየተለመደ የመጣውን “የውረድ እንውረድ ይዋጣልን” ዓይነት የልጆች ጨዋታ በምሳሌነት ይነሳል፡፡

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር ተደራጅቶ 15 ባለሞያዎችን የያዘው የመገናኛ ብዙኸን የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ሥራ ቡድን ላለፉት ስምንት ወራት በአራት አዋጆች እንዲሁም አያሌ ደንብና መመሪያዎች የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኀን ማነቆ ናቸው በሚል ለይቶ የማሻሻያ ሐሳብ ሲያዋጣ ቆይቷል፡፡

የሥራ ቡድኑ አስተባባሪ ሰለሞን ጎሹ ሲዊድን ኤምባሲ ባዘጋጀው ጉባኤ የመረጃና የመገናኛ ብዙኸን ነፃነትን የሚገድቡ፣ የበላይና የበታች ህጎች ተጣጥመው እንዲሄዱ፣ ባለቤትነት ላይ የተጣሉ ገደቦች መገናኛ ብዙኸን ነፃነቱንና ብዝኸነቱን ጠብቆ ተወዳዳሪና ጠንካራ እንዲሆን ለማስቻል ማሻሻያው ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጉ ቅጣቶች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲሁም የመገናኛ ነፃነት ላይ የሚደረጉ ገዶቦች ምን መምሰል አለባቸው የሚለውም በማሻሻያው እንደተፈተሸ ተጠቅሷል፡፡  ማሻሻያው በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ለሚንስትሮች ም/ቤት ረቂቅ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በ2012 ዓ.ም የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ከእረፍት ሲመለስም ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :