በትውልደ ኢትዮጵያውያን በመድንና በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ ተፈቀደ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Ethiopian-Diaspora-FinanceNovember 5, 2019 (Ezega.com) -- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በመድን እና በአነስተኛ ፋይናንስ ዘርፍ እንዳይሰማሩ የሚከለክለውን ህግ አነሳ፡፡ ምክር ቤቱ በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባው የመድን እና የአነስተኛ ፋይናንስ ስራ አዋጅን ለማሻሻል የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ያጸደቀው በሙሉ ድምጽ ነው፡፡

አዋጁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመድን እና በፋይናንስ ስራ ላይ እንዳይሳተፉ የተጣለውን የህግ እገዳ በማንሳት በዘርፉ መዋእለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚፈቅድ መሆኑን ታውቋል። የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያትተው አዋጁ ትውልደ ኢትዮጲያውያን በሀገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛል፡፡

አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የሚመሰርቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ ከተዘረዘሩት ስራዎች በተጨማሪ በዲጂታል ዘዴዎች የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት፣ የወኪል ባንኪንግ፣ የሐዋላ እና ከወለድ ነጻ አነስተኛ የፋይናንስ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ተፈቅዷል፡፡

ከዚህም ሌላ አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን እንደ ውጭ ሀገር ዜጋ በመቁጠር ጥሎባቸው የቆየውን የመድን እና የአነስተኛ ፋይናንስ ስራ ክልከላ በማንሳት በኢትዮጲያ ውስጥ በተቋቋመ መድን ሰጪ ወይም አነስተኛ የፋይናንስ ኩባንያ ውስጥ የአክሲዮን ባለቤት መሆን ወይም መድን ሰጪ ኩባንያ እንዲሁም አነስተኛ ፋይናንስ ኩባንያ ማቋቋም እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡

አዋጁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፋይናንስ ዘርፍ ሲሰማሩ ስለሚኖርባቸው የህግ ግዴታ እና ተጠያቀነት እንዲሁም ፈቃድ ሊያሰርዙ ስለሚችሉ ተግባራት የተዘረዘሩ መመሪያዎችን ማካተቱም በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተነግሯል፡፡

በዚህም መሰረት የውጭ ሀገር ዜግነት ላለው ትውልደ ኢትዮጲያዊ ወይም አሱ/እሷ ባለአክሲዮን ለሁኑበት ድርጅት የመድን ወይም አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም የሚከፈሉ ማናቸውም አይነት ክፍያዎች በሙሉ በብር እንደሚከፈልም አዋጁ አብራርቷል፡፡ እንዲሁም ትውልደ ኢትዮጲያውያኑ በእዚህ አግባብ የሚያገኙትን ሀብት ወይም ጥቅም ወደ ውጭ ሀገር ማዛወር እንደማይፈቀድላቸው አዲሱ አዋጅ ያስቀምጣል፡፡

በሌላ በኩል አዋጁ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ስራ ለመጀመር፣ ያላቸውን ለማስፋፋት አልያም ሌሎች ስራዎች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ሚያስችሉ የፋይናንስ ተደራሽነት መመሪያዎችንም አካቷል ተብሏል፡፡

አዲሱ አዋጅ በስራ ላይ አስቸጋሪ ሆነው አሰራሮች መካከል በአጭር ጊዜ መሻሻል የሚችሉትን በማሻሻል የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እና በመድን ስራ ላይ በተሰማሩ አካላት ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑም ታምኖበታል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ጋር ለልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር ለደቡብ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጄክት ማስፈፀሚያ እንዲሁም ከአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ጋር ለዲላ-ቡሌ-ሃሮ ዋጩ መንገድ ስራ ፕሮጄክት ማስፈፀሚያ የተደረጉትን የብድር ስምምነቶች መርምሮ አጽድቋል። እነዚህን ጨምር ዛሬ የጸደቁት ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሱ ስምምነቶች በሀገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለውን የብድር ጫና እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :