የአንበጣ መንጋው ሀገራዊ ስጋት እየሆነ ነው - የግብርና ሚኒስቴር
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 5, 2019 (Ezega.com) -- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጲያ አድማሱን በፍጥነት እያሰፋ የመጣው የበረሃ አንበጣ በሀገሪቱ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ተብሏል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ጋንታሞ እንዳስታወቁት የበርሃ አንበጣውን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉት ስራዎች እምብዛም ውጤታማ እየሆኑ አይደሉም፡፡ ለእዚህም በተለይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ዋነኛ ምክኒያት እየሆነ ነው።
ወረርሽኙ አሁንም በተለይ በአራቱ ክልሎች አስጊነቱ እንደቀጠለ ነው ያሉት ዳሬክተሩ ከባለፉት ሳምንታት አንስቶ የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች በባሕላዊ መንገድ፣ በሰው ኃይል እና በማሽን በመታገዝ የመከላከል ሥራ እየተሰራ እንደሆነ አስታወቀዋል፡፡
ምንም እንኳን ይህንን የመሳሰሉ የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የአንበጣ መንጋው አየተዛመተ ካለበት ፍጥነት ጋር ሲነጻጸር ግን ችግሩ ለሀገር የሚያሰጋበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ በአሁኑ ሰአት በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ፣ በራያ ቆቦ፣ በምስራቅ ኦሮሚያ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች በስፋት የተዛመተው የአንበጣ መንጋ ችግሩ እየተባባሰ ለመምጣቱ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡
አደጋው በስፋት በተከሰተባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች የመከላከል ስራ በመሰራት ላይ ያለ ቢሆንም ያለ ህብረተሰቡ ርብርብ ይሄ ነው የሚባል ውጤት ሊገኝ እንደማይችልም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ከዚህም በላይ ስጋቱን ያባባሰው መንጋው እስካሁን ባልታየባቸው ሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች ሊዛመት እንደሚችል ምልክት መታየቱ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የበረሃ አንበጣው በተከሰተባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በምግብ ሰብል እና በእንስሳት መኖ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ሁሉንም ዜጋ ሊያሳሳበው እንደሚገባም ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡
ሚኒስቴር መስረያ ቤቱ ችግሩን ለመቋቋምም እና የአንበጣ መንጋውን ስርጭት ለመግታት በተሸከርካሪ፣ በአይሮፕላን እና በሰው ጉልበት ታግዞ ኬሚካል የመርጨት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተሩ አመልክተዋል። ለዚህም የወሎ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል፣ የአልባሳት እና የመርጫ መሳሪያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ተብሏል።
በትግራይ ክልል ባለፈው ሳምንት ታይቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በክልሉ ወጣቶች እና በዩንቨርስቲዎች የተደረገው አፋጣኝ ርብርብ የአንበጣ ወረርሽኙን ማስወገድ ያስቻለ ሲሆን ይህም ህብረተሰቡ የጉዳቱን መጠን በመረዳት እገዛውን ቢያጠናክር የበረሃ አንበጣው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ማጥፋት እንደሚቻል ማሳያ ይሆናል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል አክለውም የአንበጣ መንጋው በንፋስ ኃይል ረጅም ርቀት የመጓዝ ችሎታ ያለው በመሆኑ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በፍጥነት ሊዳረስ ይችላል፡፡ ይህም የጉዳት ሽፋኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመምጣቱ ሌላው ምክኒያት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እስካሁን የአንበጣ መንጋው እንደ ሀገር ያደረሰው የጉዳት መጠን በሚኒስቴሩ ተጠንቶ ለህዝብ ይገለጻል ያሉት ኃላፊው ክልሎችም ቅንጅታዊ አሰራርን በመተግበር አደጋውን መከላከል እንዲሁም እየደረሰ ያለውን የጉዳት መጠን ማጥናት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በችግሩ ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተሰምቷል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን