35 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የዳያስፖራ አባላት የንግድና ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስዱ
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 18, 2019 (Ezega.com) -- በተያዘው 2012 በጀት አመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ1 ሺህ 32 በላይ ዳያስፖራዎች ከ 35 ቢሊዮን ብር የሚልቅ የካፒታል መጠን አስመዝግበው የንግድና ኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ይህንን ያለው ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ውይይት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት እና የቀጣይ ጊዜያት እቅዶች ላይ ለተሰብሳቢው ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንዲሁም የኤጀንሲው የክልል ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች እና የዳያስፖራ ማህበራት የበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቶችን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። በኤጀንሲው የዳያስፖራ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ እንዳብራሩት በተያዘው ዓመት በቁጥር በርካታ የሆኑ ዳያስፖራዎች በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች የጎላ ተሳትፎ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ የዳያስፖራው አባላት በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይም አበረታች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ በተገለጸው መረጃ መሰረትም በንግድና ኢንቨስትመንት ስም ከተመዘገበው ገቢ በተጨማሪ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ የዳያስፖራ አባለት በተለያዩ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሂሳብ ቁጥር በመክፈት ከ7 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር በላይ መቆጠባቸው ታውቋል። ይህም ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በእጅጉ የሚበረታታ ጅምር መሆኑን ያስረዱት አቶ አውላቸው ይህንኑ የዳያስፖራውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ ኤጀንሲው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የዳያስፖራ አባላት የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እና የመፍተሔ ሀሳቦችም ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዳያስፖራው መረጃዎች በዘመናዊና በተደራጀ መልኩ የመያዝ አስፈላጊትና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዳያስፖራ መረጃ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ክፍተቶች በስፋት ተተንትነዋል። እነዚህን እና ተመሳሳይ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ በኤጀንሲውም ሆነ በሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትም በተሳታፊዎቹ ተዳሰዋል። በተለይም የዳያስፖራውን መረጃዎች በዘመናዊና በተደራጀ መልኩ ለመያዝ ያስችላል የተባለለትን ፕሮግራም ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን የተመለከቱ ሂደቶች በስፋት ተብራርተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው በኤጀንሲው ኃላፊዎች እና በመንግስት አመራሮች ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካካል በዘመናዊ መልኩ ሊደራጁ ስለታሰቡት መረጃዎች አይነትና ቅድሚያ ስለተሰጣቸው የመረጃ አይነቶች፣ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ላይ የሚገጥሙ ማነቆዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመፍታት ኤጀንሲው ስለሄደበት ርቀት ማብራሪያ የሚጠይቁት ይጠቀሳሉ፡፡
ከእዚህም በተጨማሪ በክልል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች መካከል የሚታየው የአደረጃጀት ልዩነትና የአቅም ውስንነት ስለሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበራት አደረጃጀቶች ጠንካራ የሚሆንበት መንገድ በተመለከተ አስተያየቶች ቀረበው የኤጀንሲው አመራሮች እስከአሁን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይም ሁሉም የዳያስፖራ አባላት ወደ ታላቁ ቤተ መንግስት በማምራት አዲስ የተገነባውን ‹የአንድነት ፓርክ› እንዲጎበኙ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን