ሲዳማ የሀገሪቱ 10ኛው ክልል መሆኑ ተረጋገጠ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Sidama-VotesNovember 23, 2019 (Ezega.com) -- ህዳር 10, 2012 ዓ.ም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የመጀመሪያ ዙር ውጤት መሰረት ሲዳማ 11ኛው የሪፐብሊኩ ክልል ሆኖ ለመደራጀት የሚያስችለውን 98.51 በመቶ ድምፅ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡ ቦርዱ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው ለህዝበ ውሳኔው ከተመዘገበው 2.3 ሚሊዮን መራጭ ውስጥ 2 ሚሊዮን 277 ሺህ 63 ሰው ድምፁን የሰጠ ሲሆን ይህም ማለት ከተመዘገበው ህዝብ 99.86 በመቶ የሚሆነው ሰው ድምፁን መስጠቱን ያሳያል፡፡

በምርጫ ቦርዱ መረጃ መሰረት ድምፃቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከልም 2 ሚሊዮን 225 ሺህ 249 የሚሆኑት ድምጻቸውን ለ ‹ሻፌታ› ሲሰጡ ይህም ከጠቅላላ መራጩ 98.51 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡ በተቃራኒው ‹ጎጆን› የመረጠው ጠቅላላ ህዝብ ብዛት ደግሞ 33 ሺህ 463 ወይም ከጠቅላላው መራጭ 1.48 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ በዚህ መሰረት ይፋ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ የህዝበ ውሳኔው ውጤት ሲዳማ ክልል ሆኖ ለመደራጀት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን ቦርዱ አስታወቋል።

ይህ ማለት ቀድሞም እንደተገመተው ድምፅ ከሰጠው መራጭ ህዝብ ውስጥ እጅግ የሚበዛው ሲዳማ ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱን ክልል እንዲመሰርት ያለውን ፍላጎት አረጋግጧል ማለት ነው ፡፡ በመሆኑም ሲዳማ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ 10ኛው የክልል መንግስት አባል መሆኑ በዛሬው ዕለት ተረጋግጧል።

‹‹የህዝበ ውሳኔው ሂደት ሠላማዊ እና ተዓማኒ ብሎም ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ከመሆኑም ሌላ በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንድ ርምጃ ወደፊት የሄድንበት ህዝበ-ውሳኔ ነው፡፡›› በማለት የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመጀመሪያው አንስቶ እሰከ ዛሬ ድረስ የተከናወነው የህዝበ ውሳኔው ሂደትም በአጠቃላይ ሰላማዊ ፣ህጋዊ እና ሁሉን አሳታፊ እንደነበር አስታውቋል፡፡

በሌላም በኩል የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን ለማስፈፀም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የምርጫ ካርዶች እና ቁሳቁሶች መመደባቸውን ብሎም በሀገሪቱ ምርጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእዚሁ አላማ የተዘጋጁ ዘመናዊ የፕላስቲክ ድምጽ መስጫ ሳጥኖች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጉንም የምርጫ ቦርዱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በመግለጫው ማገባደጃ ላይ ቦርዱ ውጤቱን ተከትሎ ሊደረጉ ይገባቸዋል ያላቸውን ቀጣይ ተግባራት በተመለከተም ሰላማዊ እና ህግን የተከተለ አሰራር እንደሚታይ ከእዚህም በላይ የመራጩ ህዝብ ፍላጎትም እንደሚከበር ያለውን ተስፋ ገልጿል፡፡ ‹‹በውጤቱ መሠረትም በህገመንግስቱ አንቀጽ 47/3/መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና የሲዳማ ዞን አስተዳደር የህዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም የሽግግሩን ጊዜ እና ስርዐት በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የስልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንን ህዝበ-ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የጸና ዕምነት አለው።›› ብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና የሲዳማን በክልልነት የመደራጀት መብት መረጋገጥ ተከትሎ ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች በመላው ሀገሪቱ ሊቀጣጠሉ እንደሚችሉ ከወዲሁ ምልክቶች መታየት መጀመራቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ በተለይም በእዚሁ በደቡብ ክልል የወላይታ የክልልነት ጥያቄ በቅርቡ እንደሚነሳ የሚጠበቅ ሲሆን በተመሳሳይም የጉራጌ እና ሌሎች የክልሉ ዞኖችም ይህንኑ መስመር የመከተል አዝማሚያ እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሀገሪቱን ህዝቦች ከአንድነት ይልቅ ለበለጠ መከፋፋል እንዳያዳርጋቸው ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ብዙዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :