የቻይናው አሊባባ በኢትዮጲያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሊጀምር ነው
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 27, 2019 (Ezega.com) -- የቻይናው ቁጥር አንድ ቢሊየነር እና የአሊባባ መስራች ጃክ ማ ከጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ በቀረበለት ግብዣ መሰረት በኢትዮጲያ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል፡፡ ኩባንያው ካለው እጅግ የገነነ ዓለም አቀፍ እውቅና እና ስኬት አንጻር ጉብኝቱ በተለይ ሀገሪቱ የናፈቀችውን ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ለማስፋፋት አቋራጭ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡
ተስፋውን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር ያስችላል የተባለለት ስምምነትም በኢትዮጲያ እና በአሊባባ ኩባንያ መካከል በአዲስ አበባ ተፈርሟል፡፡ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንሰትሩ ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ እና በአሊባባ ኩባንያ ተወካይ አማካኝነት የተፈረመው ስምምነት ዓለም አቀፍ የኤሊክትሮኒክ ግብይትን በኢትዮጲያ ለመጀመር የሚያስችል መሆኑ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ በመርሀ ግብሩ ማስጀመሪያ የፊርማ ስነስረዓት ላይ የታደሙት ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ እንዳሉት የተደረሰው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትብብር ስምምነት ኢትዮጲያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ 5 ግዙፍ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዷ ለመሆን የያዘችውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡
በተጨማሪም ዘርፉ እንደ ኢትዮጲያ ላሉ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት እና ህዝቦቻቸው ጉልህ ጠቀሜታ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚንሰትሩ በተለይ ለመካካለኛ ኢንተርፕራይዞች ዓለም አቀፍ የገበያ እድልን በመፍጠር እድገታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ያፋጥናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው የተደረሰው ስምምነት የሀገሪቱን የግብር ስርኣት ለማዘመን ብሎም ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
የአሊባባ መስራች እና ባለቤት የሆነው ጃክ ማ በበኩሉ የኢትዮጲያ መንግስት በተለይም ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰጡት ትኩረት የኩባንያውን ቀልብ መሳቡን አንስቷል፡፡ ስለሆነም ኩባንያው ዓለም አቀፍ የኤሌክተሮኒክ ግብይትን በኢትዮጲያ ለመጀመር ወስኗል ሲልም አክሏል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጲያ በመንግሰትም ይሁን በግሉ ዘርፉ የምታመርታቸውን ምርቶች በአሊባባ ኩባንያ የኤሌክተሮኒክ ግብይት ዘዴ አማካኝነት በቀላሉ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚያስችላት ተነግሯል፡፡ ከእዚህም በተጨማሪ ጃክ ማ እና የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተለያዩ ተቋማት እና በዘርፉ የኢትዮጲያን እንቅስቃሴ የሚያሳዮ ተግባራትን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ ሌሎች ተጨማሪ ስምምቶችንም ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተሰምቷል፡፡
የአሊባባ መስራች እና ባለቤት ጃክ ማ በአሁኑ ወቅት በቻይና ቁጥር አንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ቁጥር ሃያ ቢሊየነር ሲሆን የተጣራ 39.7 ቢልዮን ዶላር የሚደርስ ሀብት እንዳለው ይነገራል፡፡ ቻይና የ "ቢዝነስ አምባሳደሬ" ብላ በኩራት የሰየመችው እና በታታሪነቱ የሚታወቀው ጃክ ማ በልጅነት እድሜው ከአሜሪካ እና ከአውሮፖ ወደ ቻይና ለሚሄዱ ቱሪስቶች የትውልድ ከተማው ‹ሀንግዡን› በትንሽ ክፍያ በማስጎብኘት የጀመረው የቢዝነስ እንቅስቃሴ አሁን ላይ በአመት ከ56 ቢልዮን ዶላር በላይ የሚያተርፈው የአሊባባ ግሩፕ ሆልዲንግ ኩባንያ ባለቤት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የእዚህ ስኬታማ የፈጠራ ሰው ጉብኝት በኢትዮጲያ ላሉ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች እና እለት እለት የውጥረት ዜና በማይለያቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ የነገ የሀገሪቱ ተስፋዎች አንዳች የመነሳሳት እና ለበጉ ተግባር የመጽናት ተሞክሮን ሊያመላክት እንደሚችል ይታመናል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን