የሀገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Inflation-EthiopiaDecember 4, 2019 (Ezega.com) -- በኢትዮጲያ በተለይ ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋራ በተያያዘ የኑሮ ውድነቱ ከእለት ወደ እለት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ነዋሪዎች በምሬት ያነሳሉ፡፡ የሚመለከታቸው የፌደራል መንግሰት እና የክልል መስተዳድር አካላት ለችግሩ እልባት ለመስጠት እየሰራን ነው የሚል ተደጋጋሚ ምላሽ ሲሰጡ ቢቆዩም ነገሮች እየተባባሱ መምጣታቸው እየታየ ነው፡፡ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዛሬ ይፋ ያደረገው መረጃም ይህንኑ ያረጋጋጠ ሆኗል፡፡ በተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ የሆኑት አቶ አማረ ለገሰ በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው እንደተናገሩት በኢትዮጲያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በተለይ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቶ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ 18.6 በመቶ ደርሷል፡፡ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ጭማሪው አጠቃላይ የምርት እና የአገልግሎት የዋጋ ግሽበት ያስከተለ ቢሆንም የዋጋ ንረቱ በከፍተኛ ደረጃ ያየለው ግን በተለይ ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች ላይ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች የዋጋ ግሽበት አስደንጋጭ በሆነ መጠን ጨምሮ 23.2 በመቶ ላይ መድረሱን አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ የምርትና የአገልግሎት የዋጋ ግሽበት መጨመር የጀመረው ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ነው ያሉት ኃላፊው የዋጋ ንረቱ ከባለፈው ሐምሌ ጀምሮ እስከ ጥቅምት ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ ማሳየቱን አንስተዋል፡፡ የሐምሌ ወር የዋጋ ግሽበት 15.5 በመቶ የነበረ ሲሆን የወሩ የምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች እና አገልግሎቶች የዋጋ ግሽበት 10.3 በመቶ፣ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች ደግሞ 20 በመቶ ላይ ነበር ተብሏል፡፡ ይህ አሀዝ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች እና አገልግሎቶች የዋጋ ግሽበት 13.4 በመቶ የደረሰ ሲሆን ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች ደግሞ 23.2 በመቶ መጨመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም የሀገሪቱ አጠቃላይ የወሩ የዋጋ ግሽበት 18. 6 በመቶ ላይ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል ፡፡

ችግሩን ለማቃለል አጠቃላይ የምርት እና የአገልግሎት አቅርቦትን፣ የሀገሪቱን ተያያዥ ፖሊሲዎች እና ሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያቶችን መፈተሽ እንደሚገባ የጠቆሙት ኃላፊው በተጨማሪም በሀገሪቱ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ትክክለኛ መንስዔ በሚመለከተው አካል በጥናት ታውቆ አፋጣኝ የማስተካከያ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባውም አስረድተዋል፡፡

ተደጋግሞ በመንግሰት አካላት አና በአንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች እንደሚባለው አሁን በሀገሪቱ ለተከሰተው የዋጋ ንረት ዋነኛ መንስኤው በምርት ስፋት፣ በአገልግሎት አቅርቦት እና ፍላጎት መካካል እየጨመረ የመጣው ሰፊ ክፍተት ነው፡፡ ለምርት አቅርቦቱ እና ፍላጎቱ አለመጣጣም ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው የሚፈጠረው የሰላም እና የመረጋጋት እጦት የመጀመሪያው ምክኒያት እየሆነ መምጣቱም ይነገራል፡፡ አለመረጋጋቱ እነዚህ ምርት እና አገልግሎቶች ከቦታ ወደ ቦታ በተፈለገው ብዛት እና ፍጥነት እንዳይዘዋወሩ ከማድረጉም በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዳይገባ እንቅፋት እየፈጠረ በመሆኑ የካፒታል እጥረት በመፍጠር በቂ የውጭ ምንዛሬ እንዳይገኝ ማነቆ እየሆነ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡ በእዚህም የተነሳ ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር እየተከሰተ፣ የፋብሪካ ምርቶች እየቀነሱ እና የሀገሪቱም የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲባባስ እየሆነ በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡

ከእዚህም ባለፈ መንግስትን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የክልል የስራ ኃላፊዎች ለፖለቲካው የሰጡትን ትኩረት በማለዘብ የህዝቡን ኑሮ ለማቃለል እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲረጋጋ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የብዙዎች ሀሳብ ነው፡፡   

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :