ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን በኖርዌይ ተቀበሉ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Nobel-Peace-Prize-AbiyDecember 10, 2019 (Ezega.com) -- ባሳለፍነው መስከረም ወር የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኖርዌይ ኦስሎ በተደረገ ደማቅ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ በተከናወነው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ዘለግ ያለ ንግግርም አድርገዋል። በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካካል የተካሄደውን ጦርነት በማንሳት እና ስለ ሰላም አስፈላጊነት በማብራራት ንግግራቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ “ሰላም እንደ ዛፍ ችግኝ ነው ችግኝን ተክሎ ለማሳደግ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላምም ጥሩ ልብ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ዛሬ እዚህ ቆሜ ስለ ሰላም የምናገረው የእድል ጉዳይ ሆኖ ነው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሲጀመር ወጣት ወታደር ነበርኩ የጦርነትን አስከፊነትን በአካል ተገኝቼ «ወንድም ወንድሙን ሲገድል» ተመልክቻለሁ ያሉት ዶ/ር ዐብይ ጦርነትን ያላዩ በደፈናው ግን የሚያወድሱት ሰዎች አሉ እነዚህ ሰዎች በጦር ሜዳ ያለውን እልቂት፣ ውድመት እና የልብ ስብራት ስላላዩት ነው ብለው እንደሚያስቡም አስረድተዋል፡፡

በንግግራቸው ፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂን ያሞገሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ «ይኽንን ሽልማት የምቀበለው በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን ስም ነው። በተለይ ደግሞ ለሰላም ሲሉ ከፍተኛውን መስዋእትነት በከፈሉት ዜጎች ስም›› ከማለታቸውም በላይ ‹‹በተመሳሳይ ሽልማቱን የምቀበለው በአጋሬና የሰላም ጓድ በኾኑት ፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ስም ነው» ብለዋል። የፕሬዝዳንት ኢሣያስ መልካም ፈቃድ፣ እምነት እና ቁርጠኝነት በሃገሮቻችን መካከል የዘለቀው መቆራረጥ እንዲያበቃ ወሳኝ ነበር ሲሉም አክለዋል። በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት የሰላም ሂደት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ባብራሩበት የንግግራቸው ክፍልም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ሙሉ በሙሉ እንደ አዲስ መጀመሩን፣ የአየር እና የቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነት እንዲቀጥል መደረጉን እና ቀሪ ጉዳዮች ላይም ውይይቱ መቀጠሉን አስታውቀዋል። በመሆኑም ሀገራቱ ጠላቶች እንዳልሆኑ ይልቁንስ ድህነት የጋራ ጠላታቸው እንደሆነ በመረዳት ለሁለቱ ሀገራት እና ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ብልጽግና መስራት መጀመራቸውንም ተናግረዋል። “በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደር” የሚለውን አባባል በማንሳት የአንዱ ሰላም ለሌላው አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልእክትም ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት መረጋገጥ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንስራ የሚል ጥሪን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመድረኩ ላይ ስለ መደመር ጽንሰ ሀሳብም ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን መደመር ሀገር በቀል ሀሳብ እና የጋራ ብልጽግና ላይ ያተኮረ ፍልስፍና መሆኑን ተናግረዋል።“በመደመር ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ እኛ እና እነሱ የሚል ነገር የለም በመደመር ውስጥ እኛ እና እኛ ብቻ ነው ያለው” ሲሉም ተደምጠዋል። ከእዚሁ ጋር በማያያዝ እርሳቸው ከ 18 ወራት በፊት ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ተከናውነዋል ያሏቸውን ተግባራትም ለታዳሚው በዝርዝር አሰምተዋል፡፡ «ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈትተናል፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጸሙባቸው ማሰቃያዎችን ዘግተናል አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም ለእውነተኛ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ መሰረቱን ያደላደልን ስለሆነ በቅርቡም ነጻ እና ፍትኃዊ ምርጫን እናካሂዳለን» ያሉ ሲሆን ለእነዚህ ጥረቶች ስኬት የጽንፈኝነትን እና የከፋፋይነትን መንገድ ማስወገድ እንደሚገባም አስምረውበታል።

በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክተው ባሰሙት ንግግር ደግሞ የዓለም ሀያላን ሀገራት በአካባቢው ጦራቸውን እያሰፈሩ መሆኑን በማንሳት እንዲሁም አሸባሪዎች በስፍራው ለማንሰራራት የሚያደርጉትን ጥረት በመጥቀስ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የሰላም እና የብልጽግና ማዕከል ኾኖ በሌሎች አፍሪካ ሃገራት በአብነትነት ሲወሰድ ማየት እንደሚመኙ ተናግረዋል።

በስነስርዐቱ ላይ ስለ ሽልማቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሸናፊ ስለሆኑባቸው ምክኒያቶች ያብራሩት የኖቤል ኮሚቴው ሊቀ መንበር ቤሪት ሬይስ አንደርሰን ስለኢትዮጲያ የብዙዎችን ስሜት በነካ ሁኔታ እንዲህ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ሰዎች ከአፍሪካ ቀንድ መልካም ዜና ተሰምቶ አያውቅም ይላሉ ነገር ግን ታሪክን ስናጠና በእርግጥም በርካታ የምስራች ከአፍሪካ መጥቷል፡፡ ኢትዮጲያ የሰው ዘር መገኛ ሀገር ናት በዚህ መሰረት እኛ ሁላችንም ኢትዮጲያውያን ነን ማለት ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሀገርዎ የተለየ ታሪክ ባለቤት ናት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ በጭራሽ በምእራባውያን ቅኝ አልተገዛችም ለእዚህም ነው የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው፡፡››

በኦስሎው ስነስርዐት ላይ ኢትዮጲያውያን አርቲስቶች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የታደሙ ኢትዮጲያውያንም ጠቅላይ ሚንስትሩን በማቀፍ እና በመሳም ደስታቸውን ሲገልጹላቸው ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትናንት ምሽት በኖርዌይ የኖቤል ተቋም የክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውም የሚታወስ ሲሆን በመዝገቡ ላይ በአማርኛ አስተያየታቸውን በማስፈርም የመጀመሪያው ሎሬት መሆናቸውን የኖቤል ተቋሙ መረጃ ያመለክታል፡፡

የሽልማቱ ስነስርአት ለመመልከት እዚህ ይጫኑ

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :