ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሚያስፈልገው ገንዘብ 60 በመቶው ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ተገኝቷል - ገንዘብ ሚኒስቴር

ኢዜጋ ሪፖርተር

WB-IMF-EthiopiaDecember 12, 2019 (Ezega.com) -- ኢትዮጵያ ለቀረጸችው የሶስት ዓመት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ማስፈጸሚያ ከሚያስፈልጋት 10 ቢሊየን ዶላር ውስጥ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለመሸፈን መስማማታቸው ተነገረ። የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንዳስታወቁት ለአጠቃላይ ሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራው ትግበራ በሶስት ዓመታት ውስጥ 10 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ትልቁን ድርሻ ማለትም ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን ለመሸፈን ተስማምተዋል፡፡ ‹‹ከሁለቱ ተቋማት ጋር ተግባብተን የሀገር በቀሉን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ በተለየ ሁኔታ የሀብት ማሰባሰብ ስራ ተሰርቶ ይሄንን ለመደገፍ ተስማምተው ነው ያሉት ነገር ግን የመጨረሻው ‹አፕሩቫል› በሚቀጥለው ሳምንት ወይም ሁለት ሳምንት ውስጥ የሚያልቅ ይሆናል ለቦርድ ቀርቦ›› በማለት ሚንስትር ዲኤታው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ይህንን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት መቻሉ ተቋማቱ በፕሮግራሙ ላይ ያሳደሩትን እምነት ያሳያል ያሉት ኃላፊው ቀሪውን ገንዘብም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሀገሪቱ ዘላቂነት ያለው እና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዕቅድ ነው በማለት በቅርቡ ይፋ ያደረገችው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር በዋናነት የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፉን ማሻሻል፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እና የእዳ ጫናን መቀነስ ላይ ያተኮረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእዚህም በተጨማሪ የወጪ እና ገቢ ንግዱን ሚዛን ማስጠበቅን ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫው አድርጓል:: ከማሻሻያ ስራዎቹ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን የሰጡት ሚንስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ በሀገሪቱ የፋይናንስ ስርአት ውስጥ የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል የገንዘብ ፖሊሲው መሻሻሉን እና የገቢ አሰባሰቡም ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የግል ባንኮች ሲያበድሩ ከብሄራዊ ባንክ የሚገዙት የ27 በመቶ የግዴታ የቦንድ ግዢ እንዲቀር በመደረጉ ባንኮቹ የብድር ወለድ መጠንን መቀነስ ጀምረዋል መንግስትም ያሰበውን አላማ አንደሚያሳካ ምልክቶች ታይተዋል ተብሏል። ‹‹ከእዚህ በፊት የግምጃ ቤት ሰነድ በቁንጽል ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የተተወውን ለገበያ ክፍት እንዲሆን በማድረግ ባለፈው ዕሮብ የተደረገው የመጀመሪያው ውድድር ያለበት የግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ በጣም አበረታች ውጤት ነው ያስገኘው፡፡ 9 ባንኮች የተሳተፉበት ወድድር ያለበት እና እንደፈለግነው ከእዚህ ተነስተን ወደ ስቶክ እና ካፒታል ማርኬት ለማስኬድ የሚያስችለን ጥሩ ብርታት የሆነን ስራ ነው የተሰራው፡፡›› በማለትም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ከእዚህም በተጨማሪ የቁርጥ ግብር መስተካከሉን እና የቅንጦት እቃዎች ላይ የሚጣለው ቀረጥ (ኤክሳይስ ታክስ) ማሻሻያ ተደርጎበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚፀድቅ ያስታወቁት ሚንስትር ዲኤታው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በማሰብም የግብርና መሳሪዎች ያለቀረጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በገንዘብ ሚኒስቴር የተፈቀደ ሲሆን በእዚህም ምክኒያት አሁን በርካታ ትራክተሮች እና ኮምባይነሮች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ‹‹የሀገራችን የእርሻ ማሳዎች የትራክተር ድምጽ የሚሰሙበት ጊዜ መጥቷል፡፡›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በስኳር፣ በቴሌኮም፣ በሃይል ዘርፍ፣ በባቡር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በሎጂስቲክ ዘርፎች የተጀመረው ተቋማትን ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ወደ ግል ይዞታነት የማዞሩ ተግባርም በፍጥነት እና በጥንቃቄ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኃላፊው አረጋግጠዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :