በተቋማቱ ውዝግብ የታገተው የባቡር ፕሮጀክት በጠ/ሚንስትሩ መፍተሄ አገኘ
ኢዜጋ ሪፖርተር
December 13, 2019 (Ezega.com) -- በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል በተፈጠረ ውዝግብ አገልግሎት መጀመር የተሳነው ግዙፉ የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ -ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጣልቃ ገብነት ውሳኔ ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡ በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫዎች ከ5 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መስመር ለመዘርጋት በጠቀመጠው የዕድገት እና ትራንስፎረሜሽን ዕቅድ መሰረት ግንባታዉ ከ 4 ዓመታት በፊት የተጀመረዉ የአዋሽ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተጠናቋል፡፡
ያም ሆኖ ለርክክብ እና ለአገልግሎት የተዘጋጀው ይህ የ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት በዋናነት በኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር የተነሳ እስካሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት ሳይችል ቀርቷል፡፡ የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ችግሩ የተፈጠረው ኃይል አቅራቢው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለተደጋጋሚ ጥያቄያችን ምላሽ መስጠት ስላልቸለ ነው በማለት ይከሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለመስመር ዝርጋታው የሚያስፈልገውን ክፍያ እንዲፈጽም በቃልም በደብዳቤም መጠየቁን እና ተቋሙ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱን በእዚህም የተነሳ ስራው ሊሰራ አለመቻሉን ይናገራል፡፡ በመሆኑም ሁለቱ ተቋማት ለፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ያለብኝ እኔ አይደለሁም በሚል በፈጠሩት ውዝግብ የተነሳ የባቡር መስመሩ ታግቶ ቆይቷል፡፡
አሁን ግን በሁለቱ የመንግስት ተቋማት መካከል ረዘም ላለ ግዜ በዘለቀው እሰጣገባ ምክንያት ኃይል ባለማግኘቱ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ያልቻለው ይህ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ለቀሪ ስራው መሸፈኛ የሚሆን ወጪ ከመንግስት ግምጃ ቤት እንዲመደብለት እና ለኃይል ማገናኛ መስመሮቹ የሚውል ቁሳቁስ እንዲቀርብለት ለእዚህም በፍጥነት የግዢ ጨረታ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ወጥቶ ስራው እንዲጀመር ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ውሳኔው በጠቅላይ ሚንስትርሩ እና በሚመሩት ጽ/ቤት አማካኝነት ከተደረገው እና ሁለቱን የመንግስት ተቋማት ከሳተፈው ድርድር በኃላ የተፈላለፈ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ከአዋሽ - ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ ለተገነባው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የኃይል ማስተላለፊያ ከፍተኛ መስመሮች ዝርጋታ የሚያስፈልገው ከ37.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ከገንዘብ ሚኒስቴር ካዝና ወጥቶ እንዲከፈል የተስማሙት ተወያዮቹ ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በእዳ መልክ ተይዞ ወደፊት በሚገለጽ የጊዜ ሰሌዳ መሰርት እዳውን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዲከፍል የሚል ውሳኔም አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጲያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዋሽ-ኮምቦሎቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዱልከሪም መሀመድ በአንድ ወቅት እንዳስታወቁት የኃይል ይለቀቅልን ጥያቄውን በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ቢያቀርቡም ምላሽ ማግኘት አለመቻላቻውን እና በእዚህም የተነሳ አንዳንድ የፕሮጀክቱ አካላት ለዝገት እና ለብልሽት እየተዳረጉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ከእዚህም በተጨማሪ የተደራጀ የንብረት ስርቆትም ለእዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ሌላው ከባድ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ የስራ ተቋራጩ የያፒ መርከዚ ኩባንያ ስራ አስኪያጅም ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ለሁሉም በመጨረሻ የተደረሰው ስምምነት በተባለው ሁኔታ እና በአጭር ግዜ የሚተገበር ከሆነ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ እዳ የዳረገው የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ -ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ትንሳኤውን የሚያገኝ ይሆናል፡፡
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን