የልማት ድርጅቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዘዋወር (ፕራይቬታይዜሽን)፤ ምንነቱና ውዝግቦቹ

በሠላም ዓለሙ

Privatization-EthiopiaDecember 21, 2019 (Ezega.com) -- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ኃላፊነቱ ብቅ ሲል አሳካለሁ ብሎ ከወጠናቸው ስራዎች መካከል ፊት ተጠቃሽ ነው፤ ፕራይቬታይዜሽን፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግሉ ክፍለ ምጣኔ ሀብት ማዞር ወይም ፕራይቬታይዜሽን ከመጋቢት 2010 ዓ/ም ወዲህ መንግስት መውሰድ የጀመረው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አካልና ቀዳውሚውም ነው፡፡ ሆኖም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት መንግስት በበላይነት የያዛቸውን የልማት ድርጅቶቹን ለምን ለመሸጥ ገለገ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ በተለይም የፕራይቬታይዜሽኑ አካሄድ እንደ ዓለም ባንክ ባሉ ተቋማት የቀረበ የርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ውጤት ነው የሚቃወሙት የዘርፉ ተንታኞች አልጠፉም፡፡ መንግስት በበኩሉም ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉና በከፊል ለማዘዋር ሲወስጥን ጥቂት የማይባሉ ምክንያቶች እጁን እንደጠመዘዙት ይናገራል፡፡ ያም ሆነ ይህ መንግስት በውሳኔው ፀንቶ በእስካሁን ሂደቱ፤ የቴሌ ኮሚኒኬሽን ዘርፉን የሚያስተዳድር የህግ ማዕቀፍና ባለስልጣን መ/ቤትም አቋቁሟል፤ ዘርፉንም ሁለት ተፎካካሪ ኩባንያዎች እንዲቀላቀሉት ውሳኔ አሳልፏል፤ ስድስቱ ስኳር ፕሮጀክቶችን ለገበያው ክፍት እንደሚድርግም ተናግሯል፡፡

የፕራይቬታይዜሽን ተቃርኖ

ከወራት በፊት ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የተሰኘው ተቋም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ያደረገ መድረክ አሰናድቶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ፕራይቬታይዜሽኑ ቆም ተብሎ በደንብ መጤና አለበት እያሉ ሲከራከሩ የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት እና የኢኒሺዬቲቭ አፍሪካ መሥራችና ኃላፊ አቶ ክቡር ገና፤  የሉዓላዊነትን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ለሽያጭ ገበያ የወጡት በተለይም ኢትዮ ቴሌኮምን የመሳሰሉ ነባርና ውጤታማ ድርጅቶች ሉዓላዊነት ሥጋት ላይ የሚጥሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

መንግስት የልማት ድርጅቶቹን ገምግሞ አትራፊውን ከአክሳሪው ሳይለይና መፍትሄዎችን ሳያበጅ በጅምላ ለማዘዋወር መወሰኑ ተገቢ አይደለም ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ኢትዮ ቴሎኮምን በማሳያነት ያነሱት አቶ ክቡር፤ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሲወተውቱ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ክቡር ገና ከዚህ እርምጃው ላይ ከመድረስና ከመወሰኑ አስቀድሞ መሰራት የነበረባቸው ስራዎች ነበሩ ይላሉ፡፡ ለአብነትም ከፖሊሲ ለውጥ ጀምሮ የኢንዱስትሪ ማሻሻያዎች እና ማስፋፋት ላይ ላለመድከም ሲባል ሸጦ መገላገልን መንግስት እንደ አማራጭ ወስዷልም ሲሉ አቶ ክቡር ገና ተችተሉ፡፡

የዘርፉ ሙህራን ኢትዮጵያ እንደ አለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) በመሰሉ ተቋማት ማለትም የምዕራባዊኑ ግፊት በሯን ብትከፍት ሉዓላዊነቷን እንደማስደፈር ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ የሚያነሱት የኢኒሺዬቲቭ አፍሪካ መሥራችና ኃላፊ አቶ ክቡር ገና፤ ቻይናን እና ሩሲያን በማንሳት ሁለቱ ሀገራት በርካታ አስርት ዓመታት በፊት የመረጧቸው መንገዶች ሀገራቱ አሁን ላሉበት ምጣኔ ሀብት ሁኔታ ዋልታ ነው ይላሉ፡፡ ሩሲያ 11 ሽህ የመንግስት ድርጅቶችን ስትቸበችብ ቻይና አሻፈረኝ ማለቷ፤ ዋጋውን ሁለቱም ሀገራት ዛሬ ላይ አግኝተዋል ሲሉ በኢትዮጵያ ሊከሰት ይችላል የሚሉትን አደጋ ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ቆም ብላ ማሰብ አለባት ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩት የዘርፉ ባለሞያዎች የፈሰሰ ውሃ አይታፈስምና ሲሉ መንግስትን ያሳስባሉ፡፡

አንዳንድ የዘርፉ ባለሞያዎች የመንግስትን ውሳኔ ባይተቹም፤ ፕራይቬታይዜሽኑ ለምን አስፈለገ? የትኞቹ? እንዴትስ? ምንን ለማሳካት? የሚሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ግን አፅንኦት ይሻቸዋል ባይ ናቸው፡፡

የመንግስት እጅ ጠምዛሽ ምክንቶች

መንግስት የልማት ድርጅቶችን ለመሸጥ ሲወስን ከመሬት ተነስቶ አለመሆኑን ይናገራል፡፡ ይልቁንስ እጁን የጠመዘዙ ምክንያቶች ስለመኖራቸው አስረግጦ ይናገራል፡፡

የልማት ድርጀረቶቹ በምርታማነት ድክመታቸው፣ በሀገሪቱ ላይ ያደረሱት የብድር ጫናና ያስከተሉት ኪሳራ ፣ ሀገሪቱን ለተከማቸና ለከፍተኛ የውጭና የሀገር ዕዳ መጣል እና መሰረተ ልማት ለማስፋፋትና የገበያ ድርሻቸውን ለማሳደግ የተጨማሪ ካፒታል እጦት እንዲሁም ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚሉት ከእጅ ተምዛዥ ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ለእነዚህ ምክንያቶቹ መረጃ ሲያጣቀስም ባለፉት ስድስት አመታት ኢትዮጵያ ከተበደረቻቸው ብድሮች ውስጥ 48 በመቶውን የልማት ድርጅቶች ይይዛሉ፡፡ ይህ በገንዘብ ሲሰላም 25 ቢሊዮን ዶላር የመንገስት ልማት ድርጅቶች ብቻ ተበድረዋል፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽንና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ብቻ የ400 ሚሊዮን ዶላር እዳ ናላቸውን እያዞረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡ በመሆኑም የልማት ድርጅቱ ወደ ግሉ ክፍለ ምጣኔ ሀብት መዘዋወር፤ መንግስት ለእራሱም፤ ማደግ አለበት እየተባለ በተደጋጋሚ ለሚነገርለት የግሉ ዘርፍም አሸናፊነት ነው ብሎ ያምናል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ሀገሪቱን ለእዳና ለኪሳራ ዳርገዋል የሚሏቸው የልማት ድርጅቶች ተደራሽነታቸውም አናሳ በመሆኑ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት የጎዳ ነው የሚል አመክንዮ ያነሳሉ፡፡ ለዚህ ማሳያም፤  ከግማሽ የሚልቀው የሀገሪቱ ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተደራሽ አለመሆንና የቴሌ ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በከተማ አካባቢ መመስረትን ያሳያሉ፡፡

የፕራይቬታይዜሽን ጉዳይ በሀገሪቱ ከግል ዘርፍ ህልውና ጋር የሚተሳሰር ስለመሆኑ የሚያሰምሩበት ዶ/ር ብሩክ፤ የግል ዘርፍ መሪ ምጣኔ ሀብት በኢትዮጵያ ከተፈለገ ይህ እውን መሆኑ አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ወደፊትም ዲጅታል ምጣኔ ሀብትን ለመፍጠር በሯን ክፍት ማድረግ አለባይትም ይላሉ፤ ዘርፉ በስራ እድል ፈጠራ የሚኖረውን ጠቀሜታ ትልቅ መሆኑን በመግለፅ፡፡

እንደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪው ማብራሪያ መንግሥት ወደ ግል የሚዛወሩትን የመንግስት የልማት ድርጅቶች በጥንቃቄ አጥንቶ፣ ዋጋቸውን መዝኖና ተምኖ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም በሚያረጋግጥ መንገድ እየተገበረው ይገኛል፡፡  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን 13 የስኳር ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ሌሎችም በሙሉና በከፊል ለሽያጭ የቀረቡ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሂደቱንም እውን ለማድረግ የህግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ጀምሮ የሀብት ግመታና ሌሎች ጥናቶችን በማድረግ እየሰራሁ ነው የሚለው መንግስት እንቅፋቶች እንደማይለዩት እሙን ነው፡፡

መደምደሚያ

ስለፕራይቬታይዜሽኑ ግራ ቀኝ፤ የተቃውሞና ድጋፍ ድምፆች እየተስተናገዱ፤ መንግስት ግን እርምጃውን ቀጥሏል፡፡ በቅርቡም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አልተሻሻለም የተባለውን የልማት ድርጅቶች አዋጅ ለማሻሻል ወደ እንደራሴዎች ም/ቤት ልኳል፡፡ በቀዳሚነት ሚሸጡት እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ስኳር ፐሮጀክቶች የመሰሉ ድርጅቶች የይዞታና የሀብት ትመና ስራዎችን እየሰራም ነው፡፡

የሆነው ሆኖ የፕራይዜታይዜሽኑ ጉዳይ መንግስት እንደወጠነው ሀገሪቱን ከችግር የሚያወጣ፣ ከዕዳዋ ነፃ የሚያደርጋት፣ ፍትሃዊነትን የሚያሰፍን ወይስ የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሰጉት በእጅ አዙር የምንገዛበትና የሚያኮስስ፣ የሩሲያን እጣ ፈንታ የሚያከናንብ? ጊዜ ብቻ መልሱን ይሰጣል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :