መንግስትና የአለም ባንክ በሀገሪቱ የዕድገት ትንበያ ላይ አልተስማሙም

ኢዜጋ ሪፖርተር

World-Bank-cuts-growthJanuary 11, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው 2020 የሁለት አሀዝ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ በመንግስት የቀረበው ትንበያ የተጋነነ ነው ሲል የዓለም ባንክ አስታወቀ፡፡ ባንኩ ባስቀመጠው የዓመቱ ትንበያ መሰረት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው በ6.3 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ትንበያ በ2020 የሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት 10.8 በመቶ ይደርሳል ብሎ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር በ1 በመቶ ብልጫ እንደሚያሳይ ተገልጾ ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሀገሪቱ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ለማበረታታት በመንግስት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ለትንበያው መሰረት መሆናቸውን ቢገልጽም የዓለም ባንክ ትንበያ ግን መንግስት ካስቀመጠው ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት የታየበት ሆኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓለም ባንክ አዲሱ የዕድገት ትንበያ ከአንድ ወር በፊት ይፋ አድርጎት ከነበረው የ 9.0 በመቶ ዕድገትም ያነሰ ሊሆን ችሏል፡፡ በአሁኑ የተቋሙ ሪፖርት መሰረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው 2021 የ 6.4 በመቶ በ2022 ደግሞ የ7.1 በመቶ አድገት ያስመዘገባል ተብሎ ግምት ተቀምጦለታል፡፡

የዓለም ባንክ ለትንበያው ዝቅ ማለት ምክኒያት ያላቸውን ዘርዝሯል በዚህም በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መሪነት እየተተገበሩ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች የባለሀብቶችን እና የአለም አቀፍ ድርጅቶችን ቀልብ መሳቡን እና ለሀገሪቱም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማስገኘቱን ሪፖርቱ አንስቷል፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ እያስተናገደች ያለችው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ የወጭ ምርት እና ገቢ ማሽቆልቆል እንዲሁም በሀገሪቱ የተከሰተው እና በ 5 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለው የዋጋ ንረት ኢኮኖሚውን እየፈተኑት እንደሚቀጥሉ የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡ የዋጋ ንረቱ ባሳለፍነው ወር 19.5 በመቶ መድረሱንም የድርጅቱ መግለጫ ያሳያል፡፡ ባንኩ ባሳለፍነው ዕረቡ ከዋሽንግተን ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳብራራው መንግስት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በሚል እየተገበረ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የእድገት ምጣኔውን ኢንዲቀንስ ከሚያደርጉ ምክኒያቶች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡

የዓለም ባንክ ለዕድገት ምጣኔ ትንበያው ማሽቆልቆል በምክኒያትነት ካስቀመጣቸው ሌሎች ነጥቦች መካከል እየተባባሰ የመጣው የሀገሪቱ የሰላም እና የደህንነት ሁኔታ ይገኝበታል፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውሰጥ በተለይ ከማንነት ጋራ በተያያዘ በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ህይወት ከመጥፋቱም በላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ውስጥ ብቻ ከ 2.7 ሚሊዮን ዜጎች በላይ በሀገራቸው ተፈናቃይ ሆነዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በእምነት ተቋማት ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች በህዝቦች መካከል ከፍተኛ መጠራጠር እና ስጋትን ፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያዳከሙት በመመጣታቸው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በእጅጉ እየተዳከመ ይገኛል በመሆኑም በመንግስት የተተነበየውን የ10.8 በመቶ እድገት ማስመዝገብ የሚታሰብ አይመስልም፡፡ በተያያዘም ኢትዮጵያ ያለባት ከፍተኛ የውጭ ብድር ጫናም ለመጪዎቹ ዓመታት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ራስ ምታት ሆኖ መቀጠሉ እንደማይቀር የዓለም ባንክ ሪፖርት ያትታል፡፡

ሪፖርቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ስልጣኑን ከተረከቡ ወዲህ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጋቸውን አስታውሶ በተለይ የሀገሪቱን ትላልቅ የመንግስት የልማት ተቋማት ወደ ግል ይዞታነት ለማዘዋወር የተደረሰውን ውሳኔ በአድናቆት አንስቷል፡፡ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ የሀገሪቱ የቴሌኮም መስሪያ ቤት በዚሁ አግባብ ወደ ግል ይዘዋወራል ተብሎ እንደሚጠበቅም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :