ከአይኤምኤፍ ብድር ጀርባ

በሠላም ዓለሙ

IMF-EthiopiaJanuary 11, 2020 (Ezega.com) -- ባለፈው ወር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ለኢትዮጵያ የሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድር ማፅደቁ አይዘነጋም፡፡  የህዝብ ቁጥሯ አንድ መቶ አስር ሚሊዮን ይጠጋል የምትባለው ኢትዮጵያ፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት ዓለም ባንክን እና አይኤምኤፍን ከመሰሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እንዲሁም ከባለፀጋ ሀገራት ረብጣ ቢሊዮን ዶላሮችን በተለይም ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ስትበደር ኖራለች፡፡ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ለማድረግ ላይ ታች እያለች ያለችው ኢትዮጵያ ግቧን ለማሳካት የገንዘብ ፈሰስን ከተለያዩ አካላት እያማተረች ነው፡፡ ከሣምንታት በፊትም ሀገሪቱ የተዛባውን ጥቅል ምጣኔ ሀብት ለማስተካከል ሲባል ለተነደፈው የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ የሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድር አፅድቋል፡፡

እስካሁን የ26 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ ናላዋ ላይ የሚዞረው ኢትዮጵያ የአይኤምኤፍ ብድር በሸክም ላይ ሸክም እንዳይሆ በስጋት የሚያዩት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ብድሩ በአወንታዊ ጎኑ ሀገሪቱ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታታ ለማካሄድ ለመወጠነችውና እምቅ ተስፋ ለሰነቀችበት የማሻሻያ አጀንዳ ጉልህ አሻራ እንዳለው ሁሉ፤ በአሉታዊ ጎኑ ደግሞ ስጋትን ጭሯል፡፡ በተለይም ደግሞ ይህን ብድር ተከትሎ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እና ተቋማቱ የሚከተሉት መንገድ አለፍ ሲልም የገንዘብ መጠኑ ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ካላት የመበደር አቅም አኳያ ከፍተኛ መሆን ስጋትን ደርቧል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያበድረው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሀገሪቱ ካላት ከተቋሙ የመበደር አቅም በ700 በመቶ ይልቃል። ብድሩም የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱን ጨምሮ ለተለያዩ ዘርፎች ማሻሻያ የታቀደ ነው ቢባልም፤ ተቋሙ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ እጁን ያስገባል፤ ምዕራባዊያኑ ለበርካታ ዓመታት ልማታዊ መንግስት ነኝ ሲል የነበረው መንግስት ላይ የፖሊሲ ጫና ይኖረዋል የሚል ስጋትን ይዞ ከች ብሏል፡፡

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ሀገሪቱን የመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) በምጣኔ ሀብቱ ላይ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ግንባሩ በተለይም ልማታዊ መንግስት ነኝ እያለ እጁን ነፃ ምጣኔ ሀብት ትከተላለች በሚላት ሀገር የተገላቢጦሽ ስራ ሲሰራ ነበር፡፡ ለዚህም አበይት ማሳያው በበላይነት (በሞኖፖሊ) የያዛቸው እንደ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ፣ አየር መንገድ የመሳሰሉ ዘርፎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ አቋሙ ትችት ከምዕራባዊያኑ የማይለየው ኢህአዴግ፤ ዐብይ አህመድን ሊቀ መንበሩ አድርጎ ከመረጠ በኋላ መንገዱን ወደ ሌላ አቅጣጫ እየቀየሰ ነው፡፡

በወርሃ መጋቢት 2010 ዓ/ም ወደ ስልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ምጣኔ ሀብቱን ነፃ ማድረግ የተጠመደበት ዋነኛ ስራው ሆኗል፡፡ ይህም በምዕራባዊያን ሀገራት ቅቡልነትን ካጎናፀፉት ምክንያቶች መካከል በግንባር ተጠቃሽ ነው፡፡ ብዙዎች ልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ ጊዜ ማብቃቱ ለአይኤምኤፍ ብድር እንዳበቃት ያምናሉ፡፡

በዚህ የሚስማሙት የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ የመበደር አቅሟ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፤  ከሰሞኑን የጸደቀላት ብድርም ሀገሪቱ ካላት ከተቋሙ የመበደር አቅም በ700 በመቶ የላቀ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡  

ሆኖም እንደ አይኤምኤፍ አይነት ተቋማት ለሚያበድሩት ገንዘብ ለሚስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ የሀገር አቅም ወሳኝ ነው ሲሉ፤ ነፃ ምሳ የለምና ገንዘቡን ለምንና እንዴት እንደምናውለው፣ የክፍያ ሁኔታውም በደንብ መጤን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የብድሩን ሁለት አንደምታዎች ሲያብራሩ፤ አይኤምኤፍ ብድር ለመንግስት የገንዘብ ክንድ ከማዋስ ባለፈም ለውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና ተቋማዊ ድጋፍ ጠቀሜታ እንደሆነ ገልፀው፤ ገንዘቡን ለመጠቀም የተቀመጡ ሁኔታዎች መታወቅ ግን እንዳለባቸው በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡ የተቋሙ (አይኤምኤፍ) አሊያም የምዕራባዊያን የበላይነት፣ ተፅዕኖና እጅ ማስረዘም በፖሊሲ ቀረፃ ላይ የሚታይ ከሆነ የትም አያደርስም የሚሉት ባለሞያዎች፤ ሁኔታዎች በደንብ መጤን አለባቸው ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ለስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ለሀገር እድገት ሲባል የሚከወኑ ስራዎች ገንዘብ ፈሰስ ለማድረግ በራስ አቅም የማይቻል ከሆነ ብድር የውዴታ ግዴታ ነው መሆኑ አያከራክርም የሚሉት የዘርፉ ባለሞያዎች፤ በብሄራዊ ጥቅምና በሉዓላዊነት መደራደር ግን ለሀገሪቱ እንደማያዋጣ ሰምሩበታል፡፡ ሆኖም ከተቋሙ የሚቀርቡ ሀሳቦችም ቢሆኑ ከተለያየ ዘርፎች አንፃር ግራ ቀኙን ማየት ህልውና ጉዳይ ነውም ይላሉ፡፡

የዘርፉ ባለሞያዎች ብድር በኢትዮጵያ አልተጀመረም፤ ሀያላን ሀገራት ሚያደርጉት ነው ይላሉ፡፡ መሰረታዊ ነጥቡ ግን ገንዘቡትን የትና እንዴት እናውለዋለን፣ አቅምና ችሎታችንስ የሚለው ነው ይላሉ፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ ብቻም ሳይሆን ባለሞያዎች ብድሩ በሚውልበትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሂስ መስጠት አለባቸውም ይላሉ፡፡ የአበዳሪና የተበዳሪ አቅምና የቁመና ለየቅል መሆን የፖሊሲ ነፃነትን እንዳይጋፋ የሀገር ውስጥ አቅምን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ባለሞያዎች፤  በፖሊሲ ቀረጻም፣ የትኛው ዘርፍ፣ በየትኛው ፍጥነት የሚሉት ጥቄዎች መሰረታዊ ናቸው ይላሉ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ዶ/ር ነመራ ገበየሁ ብድሩ በፀደቀ ሰሞን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት እያካሄደችው ያለችው የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ከአይኤምኤፍ ድጋፍን እንድታገኝ አስችሏጻል ይላሉ፤  ቅድመ ሁኔታ እንዳልተቀመጠ በመግለፅ፡፡ ሀገሪቱም ተቋሙ የሚጠይቃቸውን ሁኔታዎች ቀድማ በማሟላቷ ከአይኤምኤፍ የቀረበላት ግዴታም የለም ብለዋል፡፡

በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በምትበደረው ገንዘብ የሚከወን አንዱ ሥራ ነው። ሆኖም ግን ይህ ውጥን በመንግስት ታሪፍ መሰረት እንኳ ልተፈታውን የውጭ ምንዛሬ ክፉኛ ጣራ ላያ ያደርሰዋል፤ ይህም ከመሠረታዊ ሸቀጦች ጀምሮ በየዓመቱ አምስት ቢሊዮን እስከሚወታበት ነዳጅ ድረስ ንረትን ያስከትላል የሚል ስጋትን ወልዷል፡፡
 
የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እና ሀገሪቱ የምትከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ የግል መዋዕለ ንዋይን በሚያግዝ መንገድ ማሻሻል ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ደህንነት ማዕቀፍን ቁጥጥር ማጠናከር የመሰሉ የብድሩ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የብድር ስምምነቱ ሲፀድቅ የድርጅቱ ተቀዳሚ ምክትል ዳይሬክተር መንግስት መር የእድገት ስልት ከገደቡ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የሆነው ሆኖ የገንዘብ ብድሩ የፀደቀላት ኢትዮጵያ፤ ገንዘቡ በምን መልኩ ወደ ታለመለት ዓላማ ይውላል? እንዴትስ? የሚለው ላይ ያሰምሩበታል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :