የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፉን አየር ማረፊያ ሊገነባ ነው

ኢዜጋ ሪፖርተር

Ethiopian-BishoftuJanuary 19, 2020 (Ezega.com) -- በአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የደንበኞች ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በአህጉሪቱ በግዝፈቱ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ አየር ማረፊያ ግንባታ ሊጀምር ነው፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ግንባታው በተያዘው ዓመት የሚጀመረው አዲሱ ፕሮጀክት 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግለት ይሆናል፡፡ በእዚህም የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ በኢትዮጵያ ካሉ ማናቸውም ፕሮጀክቶች የበለጠ በጀት የተመደበለት መሆኑ ተነግሯል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደተናገሩት ‹‹በቅርቡ አስደናቂ የደንበኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ማስፋፊያ በቦሌ አየር መንገድ አከናውነናል ይህም አየር ማረፊያውን በጣም ውብ እና ሰፊ አድርጎታል፡፡ ያም ሆኖ አሁን እያደግን ያለንበትን ፍጥነት ከግምት ስናስገባ ከ 3 ወይም ከ 4 ዓመታት በኃላ አየር ማረፊያው ሙሉ በሙሉ ይሞላል ለእዚህ ነው አዲሱን ፕሮጀክት ማንቀሳቀስ የጀመርነው›› ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ ወደ ስራ ያስገባው የቦሌው ማስፋፊያ የአየር ማረፊያውን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም በዓመት ወደ 22 ሚሊዮን አሳድጎታል በቢሾፍቱ ከተማ ልዩ ስሙ አብስራ በሚባል አካባቢ የሚገነባው አዲሱ አየር ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ በኣመት 100 ሚሊዮን የሚሆኑ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ተሰምቷል፡፡ በተጨማሪም አየር ማረፊያው በውስጡ ትላልቅ የቀረጥ ነጻ መገበያያ ሞሎች፣ ሆቴሎች፣ የማሰልጠኛ ማዕከል እና ሌሎች በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ‹‹በቢሾፍቱ 35 ካሬ ኪሎ ሜትር የሆነ ቦታ ለይተን አዘጋጅተናል ይህ ከህዳሴው ግድብ በላይ በሆነ ወጪ የምንሰራው አየር ማረፊያ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞች ያስተናግዳል ይሄ ማለት ከዱባይ አየር ማረፊያ የበለጠ ሲሆን ከሞላ ጎደል አዲሱን የኢስታንቡል አየር ማረፊያ የሚስተካከል ይሆናል›› በማለት ዋና ስራ አስፈጻሚው ተወልደ ገብረማሪያም አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን በቢሾፍቱ ለሚገነባው አየር ማረፊያ የሚያስፈልገው ወጪ ስለተገኘበት ምንጭ ዋና ስራ አስፈጻሚው ያሉት ነገር ባይኖርም የቦሌውን ማስፋፊያ ገንዘብ ካበደረው ከቻይናው ኤግዚም ባንክ ሳይገኝ እንዳልቀረ ያልተረጋገጡ ምንጮች ያወጧቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአጠቃላይ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ይጀመራል የተባለው ግንባታ አየር መንገዱ በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ አየር መንገዶች ጋር የሚያገርገውን ፉክክር በድል እንዲወጣ አስተዋጽኦ አንደሚኖረው ተነግሯል፡፡  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ዋነኛ ግብ አስቀምጦ ሲሰራበት በቆየው ‹ራዕይ 2025› በተሰኘው መሪ ዕቅድ ላይ የተካተቱ ትላልቅ መለኪያዎችን በሙሉ ከ 7 ዓመታት ቀድሞ ማሳካቱን የገለጹት አቶ ተወልደ በዚህም በተለይ ለዓለም አቀፉ የአየር ኢንዱስትሪ እጅግ ፈታኝ የነበሩትን እና በርካታ አየር መንገዶች በኪሳራ ከገበያ እንዲወጡ ያስገደዱትን ያለፉትን 10 ዓመታት በድል እና በትርፋማነት እንዲወጣ እንዳስቻለው አስረድተዋል፡፡ ‹‹ፈተናውን ተቋቁሞ መዝለቅ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብም የቻልንበት ወቅት ነው ሁሉንም የራእይ 2025 ግቦቻችንን ሙሉ ለሙሉ ያሳካነው በ2018 ነው፡፡››  

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ ይህንን ስኬት ተከትሎ አየር መንገዱ አስከ 2035 የሚቆይ ሌላ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ያስገባ ሲሆን በዋናነት አየር መንገዱ በበረራ እና በመንገደኞች ብዛት እንዲሆም በተደራሽነት ያስመዘገባቸውን እድገቶች ለማስቀጠል በሚያግዘው መልኩ የተዘጋጀ ሰነድ ነው፡፡ አዲሱ የአየር ማረፊያ ግንባታም ዋነኛው የአስር ዓመቱ ዕቅድ አካል መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ከ70 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2019 ካጓጓዛቸው 12 ሚሊዮን መንገደኞች እና 432 ሺኅ ቶን ጭነት 4 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱ ይታወሳል፡፡  

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :