ቱሪዝም፤ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ - ስር የሰደዱ ችግሮቹና የተሰጠው ትኩረት

በሠላም ዓለሙ

መግቢያ

Tourism-EthiopiaJanuary 19, 2020 (Ezega.com) -- የተባበሩት መንግስታት ድርጅትየትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ረቡዕ ታህሳስ አንድ ቀን 2012 ዓ/ም ይፋ ያደረገው መረጃ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ሀሴት ነው፡፡ ተቋሙ ይፋ ባደረገው መረጃው፣ ጥምቀትን ጨምሮ አምስት የአለም ባህላዊ ቅርሶችን በማይዳሰሱ የአለም ቅርሶች ዘርፍ፣ ‹‹በሠው ልጆች ወካይ ቅርስነት›› መመዝገቡን አስታውቋል፡፡

ከአንድ ሽህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ዘንድ በየአመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ ታውቋል፡፡ የዓለም ቅርሶችን እያጠና በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ዘርፎች መዝግቦ እውቅና የሚሰጠው ዩኔስኮ ጥምቀትን በዓል በማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገቡ ለቱሪዝም ፍሰቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው እሙን ነው፡፡

ከዳሎል እስከ ራስ ዳሸን፣ ከሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እስከ ነጭ ሳር ፣ ከወጥ አለት ከተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እስከ ሰማይ ጠቀሶቹ የአክሱም ሀውልቶች፤ ከአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት እስከ ጀጎልና የሶፍ ኡመር ዋሻ፤ ከኃይማኖታዊ እስከ ባህላዊ በዓላት፤ ጥንታዊ ስልጣኔ፤ የራስ ማንነት፤ ከ10 በላይ የስነ ምህዳር አይነት ባለቤት፤ በታሪክ ሞልታ የተትረፈረፈች ናት፤ ኢትዮጵያ፡፡ ይህም ሀገሪቷን በቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ ስለማድረጉ ይነገራል፤ ምንም እምኳ ሀገሪቱ ከዚህ እምቅ ሀብቷና ከተፈጥሮና ድንቅ ኢትዮጵያዊያን ጀባ ካሏት ገፀ በረከት አንጻር ተጠቃሚነቷ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ቱሪዝም ትኩረት ያገኘና እየተሰራበት  ኢንደስትሪ ነው፡፡ በፈረንጆቹ 2019 ብቻ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ጎብኝዎች በመላው ዓለም መንቀሳቀሳቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ አምስት በመቶው ሲሆን የኢትዮጵያ ድርሻ ግን እጅግ ዝቅተናኛ የተባለ ከዜሮ ነጥብ አምስት በመቶው በታች መሆኑን የቱሪዝም ኢትዮጵያ መረጃ ያሳያል፡፡ በሀገሪቱ ከ600 ሽህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ጎብኝዎችን ብቻ የምታስተናግድ ሲሆን ይህም ካላት አቅም አንፃር ዘርፉ አልተነካም፤ ሀገሪቱም ተጠቃሚ አልሆነችም ይላሉ የዘርፉ ተዋንያን፡፡

የዘርፉ ስር የሰደዱ ችግሮች

በቱርዝም ዘርፉ የተሰማሩ የሆቴል ባለቤቶች፣ አስጎብኝና የጉዞ ወኪሎች ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ በችግሮች ለመተብተቡ ከመሰረተ ልማት ግንባታ እስከ ሠላምና ደህንነት፤ ከተቋማት ተቀናጅቶ አለመስራት እስከ ትኩረት መነፈግ ድረስ በዐብይነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ   ፡፡      

እራሱን እንደገና እያደረጀ ያውና የስያሜ ለውጥ ያደረገው ቱሪዝም አትዮጵያ፤ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግና ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግ የማስተዋወቅና የገበያ ልማት ስራዎችን ይሰራል፡፡ ሀገሪቱ ከዘርፉ በሚፈለገውና በአቅም ልክ ላለመጠቀሟም ቱሪዝሙን የሚመሩ ፖሊሲዎችን ለማስፈፀም እዚህ ግባ የሚባል ስትራቴጂና አደረጃጀት አለመኖርን የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ግርማ በመሰረታዊ ማነቆነት ያነሳሉ፡፡ ለዚህም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም አደረጃጀት አልባነትን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

125 ሆቴሎችን በአባልነት ያቀፈውና ከተመሰረተ 22 ዓመታትን የተሸገረው የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር የሰው ኃይልን ወደ ሀብት መቀየር በተለይም የሆቴል ቱሪዝም ዘርፉ ችግር ነው ይላል፡፡ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል ለመምራትና ለማንቀሳቀስ ካለው የህዝብ ቁጥር አኳያ ወደ ሀብት መቀየር አለመቻሉን ማህበሩ በችግርነት ያነሳል፡፡

ከዚህ ባሻገርም በሰው ኃይል ልማቱ ረገድ በዘርፉ ልምድ ያካበቱ ባለሞያዎች በመንግስትም ይሁን በግሉ ዘርፍ ተሰማርተው ለቱሪዝሙ መነቃቃትን ሆነ ማደግ ድርሻቸውን እንዳይወጡ እድል አለመመቻቸት በማነቆነት የሚያነሱት የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ግርማ ናቸው፡፡

የቱሪዝም ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርት 10 በመቶ የሚሸፍንና ሌሎች ዘርፎችን በመደገፍም ዘርፍ ዘለል እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የአንድን ሀገር ባህል፣ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆ የሚያቆየው ቱሪዝም፣ የሀገሪቱን ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ ህዝብ ወይንም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎችንም ቀጥሯል፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ቱሪዝም በፈተናዎቹ ላይ ሌላ ፈተና ተደቅኖበታል፤ የሰላምና የደህንነት እጦት፡፡ ሀገሪቱ በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ለራሷ ዜጎችም ካለ ስጋት መንቀሳቀስ አላስቻለችም፡፡ በተለያዩ ክፍሎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ይዘውት የመጡት መዘዝ  ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ ጥላውን አጥልቷል፡፡ ለአብነትም በደ/ማርቆስና በይርጋአለም ውድመት የደረሰባቸውን ሆቴሎች ማንሳት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ በተሻለ ባለፉት ዓመታት ሠላም ቢኖራትም 90 በመቶው የሆቴል ቱሪዝም ገቢዋ ለቱሪስት መዳረሻዎች መተላለፊ በመሆኑ ከአንፃራዊ ሰላም እጦት ተፅዕኖ ማምለጥ አልቻለችም፡፡

መንግስትም የሠላም እጦትና አለመረጋጋት እንኳንስ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ መዋእለ ነዋዮችን ቀርቶ፤ በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት ባላቸው ባለሀብቶች ላይም ተፅዕኖው ቀላል የሚባል ስላለመሆኑ ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጫናውን ሳይድ ችግሩ ግዚያዊ መሆኑን ግን ስለመሆኑ እምነት አለው፡፡

ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ከወጪ ንግዷ በበለጠ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ያህል ገቢ ለሚያስገኝ ዘርፍ የሚመደበው በጀት አነስተኛ ሲሆን፤ በአሀዝ ለመግለፅ ያህልም ቱሪዝሙን ለሚመሩ ሰባት ተቋማት ከጠቅላላ በጀቱ አንድ መቶኛውን ወይም ግማሽ ቢሊዮን ብር የማይሞላ ነው ይላሉ ጥናት አድራጊዎች፡፡ በጀቱ አነስተኛ መሆንም ለዘርፉ መልማትም ሆነ የግብዓት አቅርቦት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ይላሉ አቶ ስለሺ ግርማ፡፡

የሀገሪቱን ጠቅላላ ምርት 10 በመቶኛ፤ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮኖችን የቀጠረ፤ በውጭ ምንዛሬ ግኝትም አንደምታው ከፍ ያለው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ፤ በችግሮች ተተብትቦ መልማት አልቻለም፡፡ ዘርፉ ሌሎች ዘርፎችን በመደገፍም ዘርፍ ዘለል ነው ቢባልም፤ የኢንቨስትመንት አማራጭ አድርጎ መዋዕለ ነዋይ ለመሳብ ስራው አልተጀመረም ይባላል፡፡ በኢትዮጵያዊን የተያዘው ዘርፉ መዋዕለ ነዋይ ለመሳብ ውጥን ውስጥ ካሉ ዘርፎች ቀዳሚ መሆኑን የሚናገራ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከትግበራ አንፃር ያን ያህል እንዳልተሰራበትም ክፍተቱን ያምናል፡፡

መፍትሄዎችና ጅምር ተስፋዎች

መንግስት በሚቀጥሉት ዓመታት የትኩረቴ ቀዳሚዎች ናቸው ብሎ ከለያቸው ዘርፎች ውስጥ ቱሪዝም አንዱ ሲሆን የተዛባውን የሀገሪቱን ጥቅል ምጣኔ ሀብት (ማክሮ ኢኮኖሚም) ለማቃናት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ዘርፉ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ገቢራዊ እንደሚደረግ በሚታመነው ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሸሻያ አጀንዳ ውስጥ ተካቷል፡፡ ቱሪዝምን ለማልማት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ተጨማሪ ማበረታቻዎችን ለመስጠት መወሰኑን የሚናገረው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ ይህም መንግስት ለሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ያነሳል፡፡

ዘርፉን ወደ ክፍለ ምጣኔ ሀብት ለማሸጋገር፣ ተቋማዊና ተዋረዳዊ ቅንጅት ለመፍጠር፣ የዘርፉን እውነተኛ መረጃ ለማወቅም የሳተላይት አካውንት መጀመር፣ ቅርስ ጥበቃና መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ይናገራሉ፡፡

ዘርፉ አሁን ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነበት ጉዳይም ዓመታዊ ገቢው ከእቅድ አንፃር ማሽቆልቆሉ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት ከታቀደው 62 በመቶው ገደማ ብቻ መሰካቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :