በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በእጅጉ አሽቆልቁሏል - የተመድ ሪፖርት

ኢዜጋ ሪፖርተር

FDI-EthiopiaJanuary 29, 2020 (Ezega.com) -- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባዔ ይፋ ያደረገው ‹‹ኢንቨስትመንት ትሬንድስ ሞኒተር›› የተሰኘው ዓመታዊ ሪፖርት በኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቅናሽ መመዝገቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ እየቀነሰ የመጣው የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መውረዱን የተመድ ሪፖርት አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 4.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ከዓለም ትልልቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገራት መካከል አንዷ እንደነበረች ያስታወሰው ሪፖርቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዘርፉ እየተዳከመ መጥቷል ብሏል፡፡

ምንም እንኳን 2016 በፊት በኢትዮጵያ ሲመዘገብ የቆየው የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ግን በአስደናቂ ሁኔታ እያደገ በመምጣት ከአህጉሪቱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሚባል መጠን ላይ ደርሶ ነበር፡፡ እስካለፈው ዓመት ድረስ በቅናሽ ውስጥም ሆኖ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መጠን ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያን ስም ያቆየው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በ2019 ያስመዘገበው መጠን ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ ከሀገሪቱ የቅርብ ዓመታት አፈጻጸም አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ቅናሽ በሚባለው ዝርዝር ውስጥ የሚካተት ሆኗል፡፡ በ2016 ከ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ብቻም ሳይሆን ከዓለም ታዳጊ ሀገራት ተርታም በቀዳሚነት ተቀምጣ የነበረችው ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ2017 ቁጥሩ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ያሽቆለቀለ የውጭ ኢንቨስተመንት ፍሰት ማስተናገዷ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የተመዘገበው አፈጻጸም ቅናሽ ቢታይበትም በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ሆኖ መቆየቱን ተመድ በጥናቱ አመላክቶም ነበር፡፡

በተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት የተካሄዱ ጥናቶችም በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ከፍተኛውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማስተናገድ ቀዳሚነቱን ይዛ የቆየችው ኢትዮጵያ ከግንባታው ዘርፍ ባሻገር በመኪና መገጣጠም እና በአነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መስክ የምታደርገው እንቅስቃሴ የቱርክን እና የቻይና ባለሀብቶችን ቀልብ መሳቡን በማገናዘብ ደረጃዋን አስጠብቃ መጓዝ እንደምትችል በተደጋጋሚ ሲተንብዩ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሀገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ክምችትም ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚደርስ ተገምቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድ እና የልማት ጉባዔ  የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት መሠረት በ2018 ወደ አፍሪካ ከመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ድርሻ ከ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ሊያልፍ አልቻለም፡፡ ያም ቢሆን በተመዘገበው አፈጻጸም መሰረት ሀገሪቱ ከአንጎላ፣ ከግብፅ፣ ከናይጄሪያ እና ከጋና በመከተል ከአፍሪካ አምስተኛዋ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር እንደተባለች ይታወሳል፡፡ እነዚህ ሁሉ ስኬቶች ባሳለፍነው 2019 ሊደገሙ አልቻሉም ያለው ሪፖርቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወርዶ ኢትዮጰያን የጎላ ቅናሽ ካስመዘገቡ ሀገሮች ተርታ አሠልፏታል ሲል አስነብቧል፡፡

ከዓለም ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገራት ተርታ በተሠለፈችበት አፍታ ከደረጃዋ እየተንሸራተተች የመጣችው ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ውስጥ ከ60 በመቶ ያላነሰው በቻይና ኩባንያዎች አማካይነት በሚካሄዱ  ፕሮጀክቶች የተያዘ እንደሆነም ሪፖርቱ ጨምሮ አመልክቷል፡፡ ለቅናሹ እንደምክኒያት የሚቀርበው በዋናነት የሰላም እና መረጋጋት እጦት መሆኑ ቢታወቅም አዲሱ የሀገሪቱ አመራርም ለኢኮኖሚው መንገራረጭ እየሰጠ ያለው ምላሽ አዝጋሚ መሆን የራሱ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡

በተመሳሳይ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በአንድ ወቅት በዘርፉ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ ትመደብ የነበረው ሞሮኮም አፈጻጸሟ ከሁለት ዓመታት በፊት ከነበረው የ3.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማሽቆልቆሉን የተመድ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ግብፅ ያሉ ሀገራት ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ ዓመቱን ማጠናቀቃቸውን የዘረዘረው ሪፖርቱ በተለይ ግብፅ ከአፍሪካ ከፍተኛ የሆነውን የኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን ማሳካቷን አስነብቧል፡፡ ሀገሪቱ ባሳለፍነው ዓመት የ5 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ወደ 8.5 ቢሊዮን ዶላር ያሻቀበ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በመሳብ በአፍሪካ በቁንጮነት ተቀምጣለች፡፡ ለግብፅ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር በሀገሪቱ የተካሄዱ የለውጥ ዕርምጃዎች ያስገኙት ውጤት እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶች በሀገሪቱ መንግስት ላይ ያደረባቸው አመኔታ እና በግብፅ የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ዋና ዋና ምክኒያት ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡

ሪፖርቱ እንዳሳየው በአፍሪካ የተመዘገበው አጠቃላይ የውጭ ኢንቨስተመንት መጠን የሦስት በመቶ ዕድገት በማሳየት ወደ 49 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በ2019 የ1.4 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ እንቅስቃሴ በማስመዝገብ ካለፈው ዓመት አንጻር ብዙ ለውጥ የሌለው አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ ለዚህ አሉታዊ አስተዋጽኦ ካደረጉት ሁኔታዎች ውስጥ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የታየው የንግድ ፍጥጫ እና ውጥረት የሚጠቀስ ሲሆን የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት እንቅስቃሴም በበርካታ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ መተማመንን ያሳጣ ክስተት እንደነበር ተነግሯል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :